​ሊጉ ላይ ዳግም ኮቪድ-19 አገርሽቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር መገባደጃ ላይ የጠፋ መስሎ የነበረው የኮቪድ-19 ቫይረስ ዳግም በማገርሸት ወሳኝ ተጫዋቾችን ጨምሮ በርካታ የቡድን አባላትን ከጨዋታ ውጪ እያደረገ ይገኛል።

በቤትኪንግ ስያሜ እየተከናወነ የሚገኘው የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የመጀመሪያውን የውድድር ዘመን አጋማሽ ፍልሚያ የፊታችን ረቡዕ እንደሚገባደድ ይታወቃል። በሀዋሳ ጅማሮውን ያደረገው ሊጉ ከመጀመሪያው ሳምንት አንስቶ በርካታ የኮቪድ-19 ኬዞች ሲያስተናግድ የከረመ ሲሆን ከ10ኛ ሳምንት ጀምሮ በድሬዳዋ በተደረጉት ጨዋታዎች ግን እስካለንበት የጨዋታ ሳምንት ድረስ (15ኛ) አንድም ኬዝ አልተገኘም ነበር። ትናንት በጀመረው የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ግን በርካታ የኮቪድ-19 ኬዞች በምርመራ እንደተገኙ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ከፋሲል ከነማ ሁለት (አንድ ተጫዋች አንድ የአሠልጣኝ ቡድን አባል) እንዲሁም ከአዳማ ከተማ በተመሳሳይ ሁለት አባላት በጨዋታው ያልተሳተፉ ሲሆን በዛሬ ሁለት መርሐ-ግብሮች ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና እና በአርባምንጭ ከተማ የማይሰለፉ ተጫዋቾች እንዳሉ ሰምተናል። በአስገራሚ ሁኔታ ነገ ከሚጫወቱት አራት ቡድኖች የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ሀዲያ ሆሳዕና፣ አዲስ አበባ እና ሲዳማ ቡና ክለቦች ጋር ቫይረሱ ተከስቷል።

በቫይረሱ የተያዙትን የቡድን አባላት ስም መግለፅ ባንችልም በአንዳንድ ክለቦች ወሳኝ ተጫዋቾች ጭምር በቫይረሱ መያዛቸውን አውቀናል። ይህንን ዘገባ በምናጠናክርበት ሰዓት ረቡዕ የሚጫወቱ ቡድኖች ምርመራ ባለማድረጋቸው በመረጃችን ውስጥ ማካተት አልቻልንም። ምርመራዎቹ ከዓርብ ጀምሮ እየተደረጉ የሚገኝ ሲሆን እንደገለፅነው ረቡዕ የሚጫወቱ ቡድኖችን ትተን ከ12 ክለቦች 8ቱ ላይ ቫይረሱ ተከስቷል።