​ፋሲል ከነማ እና ዳሽን ቢራ የአጋርነት ስምምነታቸውን አድሰዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ያለፉትን አምስት ዓመታት በጋራ ሲሰሩ የነበሩት ፋሲል ከነማ እና ዳሽን ቢራ ከፍተኛ ዋጋ በሚወጣበት አዲስ ስምምነት አጋርነታቸውን አራዝመዋል።

የአንድ ጊዜ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት የሆነው ፋሲል ከነማ ከሜዳ ላይ ብቃቱ ባለፈ ራሱን በፋይናንስ ለማጠናከር የተለያዩ የገቢ ማምጫ ሥራዎች እንደሚሰራ ይታወቃል። በዋናነትም ባለፉት አምስት ዓመታት ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ ጋር ውል አስሮ በየዓመቱ ራሱን ሲደጉም ነበር። ሁለቱ አካላት ውላቸው ማለቁን ተከትሎ ዛሬ ረፋድ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተመሳሳይ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚቆይ ውል ተፈራርመዋል። በመርሐ-ግብሩ ላይ ዳሽን ቢራ ፋብሪካን ወክለው ወ/ሪ ገነት አበበ የዳሽን ቢራ የሰው ሀይል አስተዳደር እና ኮሜርሻል ዳይሬክተር እና የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብርሃም ዘሪሁን እንዲሁም ፋሲል ከነማን ወክለው የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብርሃኑ ተገኝተዋል።

በቅድሚያ ወ/ሪ ገነት ተቋሙ የተመሰረተበትን ዓላማ ካስረዱ በኋላ ስፖርቱን ለማነቃቃት ባላቸው ፍላጎት ያለፉትን 20 ዓመታት የተለያዩ ስራዎችን እንደሰሩ አመላክተዋል። ሀላፊዋ አስከትለውም “ያለፉትን አምስት ዓመታት ከፋሲል ከነማ ጋር አብረን ሰርተናል። ከዚህም በኋላ አብረናቸው ለመስራት ተስማምተናል። ይህንን ስምምነት በደስታ ነው የተቀበልነው። ፋሲል የራሳችን ቡድን ነው።” በማለት ሀሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት አካፍለዋል።

በቀጣይ መድረኩን የተረከቡት አቶ አብርሃም በበኩላቸው “እንደ አንድ ግዙፍ የንግድ ተቋም በሀገራችን ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውም የማኅበረሰብ ድጋፍ ሥራዎች ላይ አቅም በፈቀደው መጠን በመሳተፍ ሀላፊነታችንን ስንወጣ ቆይተናል። ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥም ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ በሚችሉ ዘርፎች የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በስፋት ደግፈናል። ተቋም ያለ ህብረተሰቡ ምንም ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ያለፉትን 5 ዓመታት ከፋሲል ከነማ ጋር ሰርተናል። ፋሲል ደግሞ በአጭር ጊዜ በሊጉ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኗል። ከዚህ ጀርባ ዳሽን እንዳለ ይታወቃል። በቀጣዮቹ 5 ዓመታትም እንዴት አብረን መስራት አለብን የሚለው ላይ ተነጋግረን ተስማምተናል።” ብለዋል

የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ደግሞ ፋሲል ወደ ሊጉ ካደገበት ጊዜ ጀምሮ ላስመዘገበው ውጤት ዳሽን ቢራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን መስክረው ከፋሲል ስኬት ጀርባ ያለው ዳሽን ቢራ ፋሲልን ፈልጎ ፋሲልም ዳሽንን ፈልጎ ስምምነቱ መፈፀሙን ገልፀዋል። በንግግራቸው መጨረሻም ባለፉት ዓመታት ለተደረገላቸው ድጋፍ በክለቡ እና ደጋፊዎች ስም ለተቋሙ ምስጋና አቅርበዋል።

የስምምነት ፊርማው ከመፈፀሙ በፊት አቶ አብርሃም ገንዘብ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። በዚህም ዳሽን በ5 ዓመታት ውስጥ136 ሚሊዮን ብር የሚከፍል ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ከነበረው እና የወቅቱ ከፍተኛ ከነበረው 76 ሚሊዮን ብር ስምምነት እድገት እንዳሳየ ተናግተዋል። የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ይህ ገንዘብ እንዳለ ሆኖ ክለቡ በሚያዘጋጃቸው ኮንሰርቶች፣ ባዛሮች፣ ሩጫዎች እና የተለያዩ ዝግጅቶችም ድጋፎች እንደሚደረጉ አመላክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ክለቡ የሊጉ አሸናፊ ከሆነ 2 ሚሊዮን ብር ሁለተኛ ከወጣ ደግሞ 1 ሚሊዮን ብር በጉርሻ መልክ እንደሚሰጥ በስምምነቱ መስፈሩን ተናግረዋል።

ከመግለጫው በኋላም ሁለቱ አካላት በይፋ የስምምነት ፊርማቸውን አከናውነው መርሐ-ግብሩ ተገባዷል።