የቅዱስ ጊርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኋላ ደጀን ሳላዲን በርጊቾ በጉልበቱ ላይ ከደረሰበት ከባድ ጉዳት አገግሞ ወደ ሜዳ ለመመለስ ተጨማሪ 3 ወራት እንደሚያስፈልጉት ታውቋል፡፡ በህዳር ወር በተስተናገደው ሴካፋ 2015 መክፈቻ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ባደረገችው ጨዋታ በጉልቱ ላይ ከባድ ጉዳት ሰርሶበት ከሜዳ የወጣው ሳላዲን ከወር በፊት በጀርመን የተሳካ የጉልበት ህክምና አድርጎ ቢመለስም የቀድሞ ብቃቱን ለመመለስ ተጨማሪ 2 ወራት እንደሚያስፈልገው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡
‹‹ ህክምናው የራሱ ቅደም ተከተሎች አሉት፡፡ በካሜራ በሚታይ ማሽን ህክምና እየተደረገልኝ ነው፡፡ አሁን ጂም እና ዋና እየሰራሁ ለአንድ ወር እንድቆይ እና ከ21 ቀናት በኋላ ደግሞ ወደ እግርኳስ እንቅስቃሴ እንደምመለስ ተነግሮኛል፡፡ ከዚያም ለአንድ ወር ያህል ከኳስ ጋር እንቅስቃሴ ካደረግኩ በኋላ እስከ ግንቦት አጋማሽ ወደ ሜዳ እመለሳለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡››
‹‹ አሁን የጤንነቴ ሁኔታ በጣም ለውጥ አለው፡፡ የጨዋታ መደራረብ ለዚህ ጉዳት እንዳጋለጠኝና እረፍት ማድረግ እንዳለብኝ ተነግሮኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጀርመን ላደረግኩት ህክምና እና እዚህም ለተለያዩ ህክምናዎች ሙሉ ወጪ የሸፈነልኝና እያንዳንዱ እንቅስቃሴዬን በቅርበት ሲከታተል የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ነው፡፡ ለዚህም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በፍጥነት አገግሜ ወደ ጨዋታ በመመለስም ክለቤን ለማገልገል ጓጉቻለሁ፡፡ ››