​ሪፖርት | አርባምንጭ እና ሰበታ በሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው ጨዋታ በሁለቱ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች አርባምንጭ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።      

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተፋልመው አንድ አቻ የተለያዩት አርባምንጭ ከተማዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ከተጠቀሙት የተጫዋች ስብስብ አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው ወደሜዳ ገብተዋል። በዚህም በጨዋታው መጠነኛ የጭንቅላት ጉዳት አስተናግዶ በ57ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የወጣው ሙና በቀለን በአሸናፊ ኤሊያስ ለውጠዋል። እንደ አርባምንጭ ሁሉ በ14ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አቻ የተለያዩት ሰበታ ከተማዎችም የባህር ዳር ከተማን ጨዋታ ከቀረቡበትን አሰላለፍ በቅጣት ምክንያት ባልኖረው በረከት ሳሙኤል ምትክ ብቻ ወልደአማኑኤል ጌቱን አስገብተዋል።

በዝናባማ የዐየር ሁኔታ መደረግ የጀመረው ይህ ጨዋታ ገና ከጅማሮው መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም ገና 2 ደቂቃ ሳይሞላ አርባምንጭ አሸናፊ ኤሊያስ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በላይ ገዛኸኝ በግራ እግሩ ሞክሮት ለጥቂት በወጣው ኳስ ቀዳሚ ሊሆን ነበር። ከጨዋታው በፊት በስታዲየሙ በጣለው ከበድ ያለ ዝናብ እንዲሁም በጨዋታው በነበረው ካፊያ ሜዳው መጠነኛ ውሀ የቋጠረ ሲሆን የኳስ ቅብብሎች ክፍተትም በተወሰነ ምልኩ እንዲከሰት አድርጓል።


ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በ14ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም ፀጋዬ አበራ ኳስ ከግራ መስመር ወደ ቀኝ መስመር ሲልክ እንደ ምንም ጥሮ የተረከበው አሸናፊ ኤሊያስ ኃይለሚካኤል አደፍርስን አልፎ ጥሩ ሩጫ ካደረገ በኋላ ዘግየት ያለ ሩጫ ላደረገው እንዳልካቸው መስፍን አመቻችቶለት እንዳልካቸው ግብ አስቆጥሯል። ሰበታ ከተማ ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ቢጥሩም የኳስ ቅብብሉ ወደላይኛው ሜዳ እድገት ሳይኖረው ቀርቷል። አርባምንጭ ደግሞ በፈጣን እና ረጃጅም ኳሶች ወደ ሰበታ የግብ ክልል እየደረሱ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል። በ24ኛው ደቂቃም ልፋታቸው በሁለተኛ ግብ ሊታጀብ ተቃርቦ በላይ ከመዓዘን ምት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ቢጥርም ሰለሞን እና የግቡ አግዳሚ ተባብረው ኳሱን አምክነውታል።

እየተመሩ የሚገኙት ሰበታዎች በ28ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን አጋጣሚ የግቡ ቋሚ አምክኖባቸዋል። በዚህም ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ የጠበቀው ሳሙኤል ሳሊሶ በቀኝ እግሩ መትቶት መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሯል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሜዳው የሚፈልገውን በማድረግ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት አርባምንጮች በአንድ ጎል መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ሲሄዱ ሰበታዎች ግን ከደቂቃዎች በፊት ካደረጉት የጠራ ሙከራ በተጨማሪ በባከነው ደቂቃ በወልደአማኑኤል አማካኝ ሌላ ጥቃት ፈፅመው አቻ ለመሆን ቢቃረቡም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል።


ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ሰበታ ከተማ ካልተጠበቀ አጋጣሚ ጎል አግኝቷል። በዚህም ከመሐል መስመር በኃይሉ ግርማ ያሻገረውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ በተከላካይ ጀርባ በመገኘት በግንባሩ በመግጨት ኳስን መሬት ላይ በማንጠር መረብ ላይ አሳርፎታል። ይህኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ሰበታዎች አቻ ከሆኑም በኋላ የአርባምንጭን የግብ ክልል መጎብኘት አጠናክረው ቀጥለዋል። በአንፃሩ ብልጫ የተወሰደባቸው አዞዎቹ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የሀይል ሚዛኑን መልሰው ለማግኘት ሞክረዋል።


ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሰበታ ወደ መሪነት ሊሸጋገር ከጫፍ ደርሶ ነበር። የመሐል ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ ወደ መሐል ሜዳው ተጠግቶ የመከላከል ሀላፊነቱን ተወቶ የተቆጣጠረውን ኳስ ከርቀት በቀጥታ ወደ ሳምሶን መረብ ቢመታውም ሀሳቡን የግቡ ቋሚ አምክኖበታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዱሬሳ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ሌላ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ነበር። ከፍተኛ ብልጫ የተወሰደባቸው የመሳይ ተጫዋቾች በ84ኛው ከቅጣት ምት ሌላ አደገኛ ኳስ ተሰንዝሮባቸው ነበር። በቀሪ ደቂቃዎችም ጫናዎች ቢበረክትባቸውም ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

ወደ ጨዋታው ሲገቡ የነበራቸውን አንድ ነጥብ ከሜዳው ሲወጡ ያገኙት አርባምንጭ እና ሰበታ ከተማ በቅደም ተከተል በ18 እና 9 ነጥቦች የነበሩበት አስረኛ እና አስራ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።

                                        

ያጋሩ