[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ጥሩ ፉክክር የታየበት የምሽቱ የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሦስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሰለሞን ወዴሳ ፣ አለልኝ አዘነ እና አብዱልከሪም ኒኪማን አስወጥተው በምትካቸው መሳይ አነገኘሁ ፣ በረከት ጥጋቡ እና ኦሲ ማውሊ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ስብስብ አካል ሆነዋል። በአንፃሩ ቡናዎችም ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሦስት ቅያሬ ያደረጉ ሲሆን አበበ ጥላሁን ፣ አማኑኤል ዮሀንስ እና ታፈሰ ሰለሞን በተለያዩ ምክንያቶች አለመኖራቸውን ተከትሎ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ያብቃል ፈረጃ እና እንዳለ ደባልቄ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት መጥተዋል።
ባህር ዳር ከተማ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በኦሲ ማውሊ ፣ ፉአድ ፈረጃ እና ፍፁም ዓለሙ ባደረጋቸው ኢላማቸውን ባልጠበቁ ሙከራዎች የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አስፈሪ ነበሩ።
በአመዛኙ የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባህር ዳሮች የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ምስረታ ሂደት በማቋረጥ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ፍላጎት የነበራቸው ቢመስልም ኢትዮጵያ ቡና ከወትሮው በተሻለ ይህን ቅንጅት የሚጎድለውን ጫና በማለፍ ረገድ ስኬታማ የነበሩ ቢሆንም ኳሱን በቅብብል ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ለማድረስ በጣሙን ተቸግረው ተስተውሏል።
ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማስመዝገብ በተቸገረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአጋማሹ ሮቤል ተክለሚካኤል ከሳጥን ውጭ ካደረጋት የግብ ሙከራ በተጨማሪ በ30ኛው ደቂቃ ሀይሌ ገብረተንሳይ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ እንዳለ ደባልቄ ግጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራ አስቆጭ ነበረች።
ከዚች ሙከራ ከሦስት ደቂቃዎች በኃላ ባህር ዳር ከተማዎች ሳላዓምላክ ተገኝ ላይ ሀይሌ ገ/ተንሳይ በሰራው ጥፋት ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያገኙትን የቅጣት ምት ፍፁም ዓለሙ ሳይጠበቅ በቅርቡ ቋሚ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ የባህር ዳር ከተማው የመሀል ተከላካይ መናፍ ዓወል አቡበከሬ ናስር ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
በሁለተኛው አጋማሽ የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቂ የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻሉም ፤ በአንፃሩ ባህር ዳሮች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ጨዋታ በተመሳሳይ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በቁጥር አንሰው የኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ውስጥ መገኘታቸውን ተከትሎ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በ54ኛው ደቂቃ አሥራት ቱንጆ ከሮቤል ተክለሚካኤል የደረሰውን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም በደቂቃዎች ልዮነት አስራት ቱንጆ በግሩም ሁኔታ ከራሱ ሜዳ አጋማሽ እየነዳ ወደ ባህር ዳር ሳጥን ደርሶ ለእንዳለ ያቀበለውን ኳስ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ያበላሸው ኳስ አስቆጭ ነበር።
ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄድ ይበልጥ ወደ ግብ ክልላቸው ተስበው መከላከል የጀመሩት ባህር ዳሮች ተደጋጋሚ ጫናዎችን ራሳቸው ላይ ሲጋብዙ ተመልክተናል።
በ68ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሮቤል ተክለሚካኤል በረጅሙ ከተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ አቡበከር ናስር በግራ እግሩ በግሩም ሁኔታ አየር ላይ ከተቆጣጠረ በኃላ በድንቅ አጨራረስ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ከግቧ በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ይበልጥ ጫናቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከግቧ መቆጠር በኃላ አላዛር ሽመልስ ካደረጋት ሙከራ ውጭ አደገኛ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በአንፃሩ በጎዶሎ ተጫዋች የተጫወቱት ባህር ዳር ከተማዎች በጥሩ መከላከል አንድ ነጥቡን ይዘው ለመውጣት በቅተዋል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማዎች በ20 ነጥብ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ አንሰው 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።