ሀዲያ ሆሳዕና የተወሰነበትን ውሳኔ እንዲፈፅም ታዟል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ፌዴሬሽኑ በአክሊሉ አያናው እና ሀዲያ ሆሳዕና ዙሪያ ያሳለፈው ውሳኔ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲተገበር፤ ካልተተገበረም ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድበት አሳስቧል።

ተጫዋች አክሊሉ አያናው ቀሪ ኮንትራት እያለኝ ክለቡ ያለአግባብ አሰናብቶኛል በማለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባሳለፍነው ዓመት አቤቱታውን በማቅረቡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ወደ ሥራው እንዲመለስ እና ያልተከፈለው ደሞዝ እንዲከፈል ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ይህ ውሳኔ በመቃወም ሀዲያ ሆሳዕና ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ቢጠይቅም የቀረበውን ቅሬታ የመረመመረው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሆሳዕናን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ክለቡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፎ ቆይቷል።

ሆኖም ተጫዋቹ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ እንዲፈፀምለኝ የታዘዘው ውሳኔ ተግባራዊ አልተደረገልኝም በማለት በዚህ ዓመት ህዳር ወር ላይ በአቶ ብርሐኑ በጋሻው የሕግ አማካሪ ጠበቃ እና የአግር ኳስ ስፖርትኞች ሕጋዊ ወኪል አማካኝነት በድጋሚ አቤቱታውን ሲያሰማ ቆይቶ በስተመጨረሻም ፌዴሬሽኑ ለሀዲያ ሆሳዕና የውሳኔ ደብዳቤ ልኳል። ከሦስት ቀናት በፊት በተላከው ደብዳቤ ላይ ሀዲያ ሆሳዕና የፍትህ አካላት ከዚህ ቀደም የወሰኑት ውሳኔን ተግባራዊ አለማድረጉን በመግለፅ የውሳኔ ደብዳቤ በደረሰው በሰባት ቀን ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርግ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ይህን ውሳኔ የማይፈፅም ከሆነም ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከፕሪምየር ሊጉ ሼር ካምፓኒ አገልግሎት እንዳያገኝ እና በፕሪምየር ሊጉ ውድድር ላይም እንዳይካፈል የተወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።