የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-1 ኢትዮጵያ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አንድ ለአንድ ከተጠናቀቀው የምሽቱ የባህርዳር እና ቡና ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

የመጀመሪያው እና ሁለተኛው አጋማሽ የተለያየ ቡድን የመሆኑ ምክንያት

የመጀመሪያው አርባ አምስት የተሻለ ብልጫ ነበረን፤ በማጥቃቱ ረገደም የተሻልን ነበርን ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያው አርባ አምስት ተጋጣሚያችን ቡና አንድም ሙከራ ሳያደርግ ነበር የወጣው እና በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ተጫዋቾቼ ማድረግ ያለባቸውን ነገር አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ከመናፍ በቀይ ካርድ ከመውጣት ጋር ተያይዞ አጨዋወታችንን መቀየር እና የማጥቃት ሚዛናችንን ደግሞ ሁለተኛ አርባ አምስት ላይ ተዳክሞ ነበር። የነበረን ፍላጎት ያቺን ያገኘናትን አንድ ጎል እና ሦስት ነጥብ ይዘን ለመጠበቅ ቡናዎች የሚያገኟቸውን ክፍት ቦታዎች በመዝጋት ነበር። ግን እነሱም ጫና አሳድረው ግብ አስቆጥረውብናል፡፡ ለረጅም ጊዜ በአስር ልጅ እንደመጫወታችን ከቡና ጋር አንድ ለአንድ መውጣታችን ጥሩ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን አሁንም ያሉብንን ክፍተቶች ማረም እንዳለብን ይሰማኛል፡፡

የመጀመሪያ ዙር ግምገማ ምን ይመስላል ?

በእርግጥ በዕቅድ ካስቀመጥነው ግባችን አንፃር አላሳካንም ብዬ ነው የማስበው። ነገር ግን በመጀመሪያው ዙር ላይ በአብዛኛው ጨዋታዎች ማለት ይቻላል በጨዋታ ብልጫ ሳይወሰዱብን ነገር ግን በጥቃቅን ስህተቶች ነው ነጥብ እየጣልን የመጣነው። እነዚህን ነገሮች በሁለተኛው ዙር ላይ አስተካክለን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ። ጥሩ ትምህርት ሆኖን አልፏል ብዬ ነው የማስበው የመጀመሪያው ዙር ሁለተኛው ዙር ላይ ደግሞ በእረፍቱ ጊዜ ያሉንን ክፍተቶች አስተካክለን በጉዳት የተጎዱ ተጫዋቾች እንዲያገግሙ አድርገን ጠንካራውን ቡድን መልሰን ይዘን እንመጣለን ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው። በዚህ አጋጣሚ በድሬዳዋ ቆይታችን ጥሩ ጊዜ ነው የነበረን በፍቅር ተቀብለው በፍቅር ያቆዩንን የድሬዳዋ እና አካባቢዋ የስፖርት አፍቃሪ ህዝብ ከክቡር ከንቲባው ጨምሮ በጣም በጣም አድርጌ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነው፡፡ በተለይ እነሱ በቀይ ካርድ አንድ ሰው ካጡ በኋላ የሰው ብልጫ ስለነበር ያንን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ነበር፡፡ ያው ቁጥራቸውን አብዝተው እዛ ጋር ስለውም ስለጎደለባቸው ያን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ገምተናል። ከእረፍት በኋላ ያንን ለመጠቀም ሞክረናል ግን ያው በፈለግነው መጠን አልሄድንም፡፡

ወጣቶችን በመጠቀም የተገኘ የውጤት ግምገማ ካለ. . 

ጥሩ ነው እንግዲህ ማለት ቡና ትልቅ ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንዶቹ ተጫዋቾች ገና ልጆች ናቸው። እዚህ አይነት ጨዋታ ውስጥ ገብቶ ጫናውን ተቋቁሞ መጫወት ራሱ በሂደት ውስጥ ነው እያዳበሩ የሚመጡት። በአንድ ጊዜ ጥሩ ነው የሚያደርጉት የነበረው። የተለየ ነገር ግን አትጠብቅ፡፡

ከአምናው ውጤት አንፃር የዘንድሮ ግማሽ አመት ዝቅተኛ ስለ መሆኑ እና ስለ ነበሩ ችግሮች

ከዐምናው የተለየ ነገር የለውም። ማለት የተለየ ስል ተጋጣሚዎች የሚመጡበትን ነገር ፎርሜሽናቸውን እኛን ለመቆጣጠር የሚመጡበት መንገድ ብዙ የተለየ ነገር የለውም። ዐምና የመጡበት ነገር ነው ዘንድሮም እየመጡበት ያለው። ግን በእኛ በኩል ማድረግ የሚገባንን ነገር እያደረግን ያለን አልመሰለኝም። ልዩነቱ ያ ነው እንጂ ከተጋጣሚ አዲስ ነገር የለም የሚመጡበት ተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡

ይህን ተግባራዊ ማድረግ የከበዳችሁ ከምን የተነሳ ነው?

ከእኛ ከቡድኑ በላይ አይደለም፤ መታረም የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን ነገሮች መለስ ብለን ስናያቸው የሚታረሙ ናቸው። ስለዚህ እነዛ ለተጫዋቾቻችን እንዳይደግሙ ማሳየት እና ያንን ነገር አርመን መገኘት ነው፡፡

በሁለተኛው ዙር ከተጫዋች ግዢ እና መሰል ነገሮች መሻሻል ይኖረዋል?

አዎ እናስባለን። ካገኘን የምንፈልጋቸውን ከውል ዘመናቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ስለሆነ የምንፈልገውን ልናገኝም ላናገኝም እንችላለን ግን ሀሳቡ አለ፡፡