​ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ነገ በሚደረገው ቀዳሚው መርሐ-ግብር ዙሪያ ተከታዮቹ ሀሳቦች ተነስተዋል።

በወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች እና ሦስት ደረጃዎች ብቻ ከፍ ብለው 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም እና በመጀመሪያውን ዙር ውድድር ነጥባቸውን 20’ዎቹ ውስጥ ከቶ ወደ እረፍት ለማምራት ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይገመታል። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከአዳማ ከተማ ጋር በጣምራ አነስተኛ ጨዋታዎችን (2) የተሸነፈው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በተከታታይ ያልተሸነፋቸውን ጨዋታዎች ቁጥር ወደ ስምንት ለማሳደግ እና አዲስ አበባ ላይ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም በማግኘት ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት አጥቦ ሁለተኛውን ዙር ለመጠባበቅ ታትሮ እንደሚጫወት ይታመናል።

በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና በ14ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከወላይታ ዲቻ ጋር ተጫውቶ ሦስት ነጥብ ያስረከበበት ጨዋታ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በደካማነት ከሚያዙት መካከል አንዱ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማማሉ። ለወትሮው በአምስት ተከላካዮች ሲጫወት የነበረው ቡድኑም ወደ አራት የኋላ ተጫዋቾች ጥምረት ተመልሶ በላይኛው ሜዳ የተጫዋች ቁጥር አብዝቶ ክፍተቶችን ለማግኘት ቢያስብም ጠጣሩን የድቻ የኋላ መስመር አልፎ ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ከ62% በላይ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ኖሯቸው ጨዋታውን ቢከውኑም አብዛኛው የኳስ ቅብብላቸው በራሳቸው ሜዳ ላይ የተገደቡ እና የኋልዮሽ እንዲሁም የጎንዮሽ ቅብብሎች የበዙበት ነበር። አሠልጣኙ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እንዳሉትም ቡድኑ ላይ ሲታይ የነበረው መቻኮል ወይም ትዕግስት አልባ እንቅስቃሴ በመጠኑ ዋጋ ያስከፈላቸው ይመስላል። ይህ ከግለሰባዊ የውሳኔ አሰጣጥ ክፍተት የሚመነጨው መቻኮል ነገ ተገርቶ ካልመጣ ግን ያለፉትን ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ጎል ብቻ ያስተናገደውን የሲዳማ የኋላ መስመር መስበር ሊያቅተው ይችላል። ምናልባት በመስመር ተመላላሾች አጠቃቀም ጨዋታውን የሚጀመር ከሆነ ደግሞ አጥበው በሚጫወቱት የሲዳማ አማካዮች የሚገኘውን ሰፊ የመስመር ላይ የመጫወቻ ሜዳ በፍጥነት በማጥቃት የግብ ዕድሎችን ሊፈጥር ይችላል። በዚህም ብርሃኑ እና ኢያሱ ሜዳውን ለጥጠው አጋሮቻቸው በኪሶች ውስጥ ክፍተት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

 

በድሬዳዋ ሊጉ መከናወን ከጀመረ በኋላ የተመቻቸው የሚመስለው ሲዳማ ቡናዎች በሁሉም ጨዋታዎች አለመሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ጥሩ ባልሆኑባቸው ጨዋታዎችም ነጥብ እየያዙ መውጣታቸው ትልቅ አድናቆት ያስቸራቸዋል። በተለይ ባለፉት የወልቂጤ እና የአዲስ አበባ ፍልሚያ ቡድኑ በምርጥ ብቃቱ ላይ ባይገኝም አራት ነጥብ የግሉ አድርጓል። ከሁለቱ ጨዋታዎች ጋር ተያይዞ በእንቅስቃሴ ረገድ ፍጥነት አልባ ሆኖ የታየ ሲሆን የአማካይ መስመሩም መጠነኛ ድክመት ነበረበት። በአንፃራዊነት በአዲስ አበባው ጨዋታ ይህ ተሻሽሎ የቀረበ ቢሆንም በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት እንቅስቃሴ ግን ጥሩ አልነበረም። በአጋማሹም አንድ ብቻ ዒላማውም የጠበቀ ሙከራ እርሱንም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አድርገው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የግብ ክልል በፍጥነት ሲደርሱ ታይቷል። ይህ ቢሆንም የፊት መስመሩ የሚገኙ ዕድሎችን በአጥጋቢ ሁኔታ ወደ ግብነት የመቀየር ሌላ ችግር አስመልክቷል። የሆነው ሆኖ ቡድኑ ካስቆጠራቸው 15 ጎሎች ከ53% በላዩ ላይ ስሙ ያለው ይገዙ ነገም የትኩረት መሐከል መሆኑ አይቀርም። ከእርሱ ውጪ ፈጣኑ ሀብታሙም እንደ ሁለተኛ የሳጥን ውስጥ አጥቂ ወደ መሐል አጥቦ እየተጫወተ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሀዲያዎች ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው።

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ኮቪድ-19 በርካታ ክለቦች ጓዳ እየገባ ይገኛል። በዚህም ሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና ቤት ኬዙ በምርመራ በመገኘቱ በርካታ ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በነገው ጨዋታ አይሳተፉም። በጨዋታው የማይኖሩ የቡድን አባላትን ስም መግለፅ ባንችልም ወሳኝ ተጫዋቾች እንዳሉ አውቀናል።

አዳነ ወርቁ የነገውን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ለመምራት ሲመደብ ሙስጠፋ መኪ እና ዳዊት ገብሬ ረዳቶች ተከተል ተሾመ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– እስካሁን በሊጉ 4 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና 2 በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ሲዳማ አንዱን ሲያሸንፍ ቀሪውን አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሆሳዕና 6፣ ሲዳማ 3 ጎሎችን አስቆጥረዋል


* ከላይ እንደገለፅነው በክለቦቹ ያለውን የኮቪድ-19 ኬዝ ታሳቢ በማድረግ በዚህ ሳምንት ግምታዊ አሰላለፍ ማውጣት አልቻልንም።