[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የመሐል ዳኛው ተጎድተው በወጡበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ ሀዲያ ላይ ጣፋጭ ድል ተጎናጽፏል።
ባሳለፍነው ሳምንት የውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን በወላይታ ድቻ ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና አምስተኛ ድሉን ለማግኘት ሁለት ተጫዋቾችን ለውጦ ወደ ሜዳ ገብቷል። አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በለውጦቹ ሔኖክ አርፊጮ እና ሚካኤል ጆርጅን በፍሬዘር ካሳ እና ዑመድ ኡኩሪ ቀይረዋል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ አዲስ አበባ ከተማን አንድ ለምንም ካሸነፈበት የመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም የቡድኑ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጊት ጋትኩት እና ቴዎድሮስ ታፈሰን በግርማ በቀለ እንዲሁም ብሩክ ሙሉጌታ ምትክት በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተዋል።
ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው ይህ ጨዋታ በ10ኛው ደቂቃ ያልተጠበቀ ክስተት አስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃም የጨዋታው አልቢትር አዳነ ወርቁ የሲዳማ ቡናው የመሐል ተከላካይ ያኩቡ መሐመድ ሳያስበው ግራ እግራቸው ላይ ጉዳት አድርሶባቸው ጨዋታው ተቋርጧል። የመሐል ዳኛው ያስተናገዱት ጉዳት ጠንከር ያለ መሆኑን ተከትሎ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ተከተል ተሾመ ቦታውን ተረክቧል።
ለአራት ደቂቃዎች ጨዋታው ከተቋረጠ በኋላ ሲቀጥል በ16ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የሰላ ጥቃት ተስተናግዶበታል። በዚህም ሀዲያ ሆሳዕና በቀኝ መስመር ወደ ሲዳማ የግብ ክልል አምርቶ በሳምሶን ጥላሁን አማካኝነት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ቢጥርም የግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ ውጥኑን አምክኖበታል። ወደ መሐል ሜዳ ተጠግተው የሚጫወቱት የሀዲያ ተከላካዮች ጀርባ የሚገኘውን ጥልቀት ለማጥቃት ያሰቡት ሲዳማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እየተባሉ እንቅስቃሴያቸው ፍሬያማ ሳይሆን ቀረ እንጂ ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በ25ኛው ደቂቃ ግን ሀብታሙ በተመሳሳይ አጨዋወት ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ፈጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
አራተኛ ዳኛ የነበሩት ተከተል ወደ መሐል ዳኝነት ሲሸጋገሩ ቦታቸው ባዶ መሆኑን ተከትሎ የውድድሩ የበላይ አካል አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ቢኒያም ወርቅአገኘሁን በመጀመሪያው አጋማሽ የውሀ እረፍት እንዲመጡ አድርጎ ክፍተቱን ሸፍኗል። ፉክክር አልባው ፍልሚያ በ36ኛው መሪ አግኝቷል። በዚህም ተስፋዬ አለባቸው ከመሐል ያሻገረውን ኳስ ዑመድ ኡኩሪ ተረክቦ ሳጥኑ ጫፍ ለነበረው ባዬ ገዛኸኝ ሲሰጠው ፈጣኑ አጥቂ በግራ እግሩ ተክለማርያም ባጠበበበት ቋሚ ልኮት ግብ አስቆጥሯል። ዝግ ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የታዩት ሲዳማዎች በ40ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ ከቆመ ኳስ በሞከረው ጥቃት አቻ ለመሆን አስበው መክኖባቸዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ሙከራ ሳይስተናገድ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በ49ኛው ደቂቃ አጀማመራቸውን በግብ አሳምረው አቻ ሆነዋል። በዚህም ይገዙ ቦጋለ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በመሮጥ ግብ ለማስቆጠር ሲጥር ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ጥፋት ሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ ዳዊት ተፈራም የፍፁም ቅጣት ምቱን በጥሩ ሁኔታ በተለመደ ግራ እግሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። አሁንም የሀዲያን ግብ መጎብኘት የያዙት ሲዳማዎች በ59ኛው ደቂቃ ይገዙ የግብ ዘቡ ቦታውን ለቆ መውጣት ተከትሎ ሳይጠበቅ ከቀኝ መስመር በመታው ኳስ ሌላ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን የቀጠሉት ሀዲያዎች የኳስ ብልጫቸው ጎል ያላፈራላቸው ሲሆን ይባስ በመልሶ ማጥቃት እንዲጠቁ በር እየከፈተ ነበር። በ68ኛው ደቂቃ ግን ከቅጣት ምት ሳምሶን በመታው እና የግቡ ቋሚ በመለሰው ኳስ ዳግም መሪ ሊሆኑ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ሦስት ነጥብ እጅግ የፈለጉት ሲዳማዎች በ80ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ዳዊት ለሀብታሙ የላከውን ኳስ ሀብታሙ ግብ አድርጎት ቡድኑን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። በቀሪ ደቂቃዎች ሌላ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር በሲዳማ አሸናፊነት ጨዋታው ተደምድሟል።
ሲዳማ ቡና ስድስተኛ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 25 በማድረስ በጊዜያዊነት ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሦስት ነጥብ ያስረከበው ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ በ17 ነጥብ ያለበት 11ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።