ሪፖርት | ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን አጠናክረዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኮቪድ መነሻነት ወሳኝ ተሰላፊዎቹን ሳይዝ ወደ ሜዳ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመመራት ተነስቶ አዲስ አበባ ከተማን በመርታት ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኃላ ወደ ድል ተመልሷል።

አዲስ አበባ ከተማዎች በሲዳማ ቡና ከተሸነፈው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሮቤል ግርማ እና ዋለልኝ ገብሬ ወጥተው በምትካቸው ልመነህ ታደሰ እና ኤልያስ አህመድገብተዋል። በኮቪድ 19 ክፉኛ ስብስባቸው የተመታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያለ ዘሪሁን ሸንገታ ባደረጉት ጨዋታ አራት ለውጦችን ሲያደርጉ ምኞት ደበበ ፣ ሄኖክ አዱኛ ፣ ቸርነት ጉግሳ እና አቤል ያለው ወጥተው ደስታ ደሙ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አዲስ ግደይ በምትካቸው ገብተዋል።

ጨዋታውን ድፍረት በተሞላበት መንገድ የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶችን ወደ ራሳቸው የሜዳ አጋማሽ እንዲገፉ በማድረግ ጥሩ የሚባል አጀማመር ማድረግ ችለዋል። በተለይም ከግራ መስመር መነሻውን ያደረገው ፍፁም ጥላሁን በተደጋጋሚ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ሲፈትኖ አስተዉለናል። በ18ኛው ደቂቃ ላይም ቻርልስ ሪባኑ በረጅሙ የላከውን ኳስ ሱሌይማን ሀሚድ ማቋረጥ አለመቻሉን ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ ልኮት በሉኩዋጎ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው እንዳለ ከበደ ኳሷን አስቆጥሮ አዲስ አበባን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ አዲስ አበባ ከተማዎች ድፍረታቸውን ቀነስ አድርገው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ጠጋ ብለው መከላከል መጀመራቸውን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሂደት ወደ ጨዋታው መግባት ጀምረዋል። በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአጋማሹ በረከት ወልዴ በ25ኛው እና 36ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ በቀጥታ ወደ ግብ የላካቸው እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከርቀት የመቷቸው እና ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጡባቸው ኳሶች ውጪ ጋቶች ፖኖምም እንዲሁ በግራ እግሩ ከሳጥን ውጭ ያደረጋት እና ዳንኤል ተሾመ በግሩም ሁኔታ ካዳነበት ኳስ ውጭ በእንቅስቃሴ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በረጃጅም እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት የነበራቸው ፍላጎት ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን አዲስ አበባዎች ደግሞ ይበልጥ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው የተጫወቱበት አጋማሽ ነበር። በ67ኛው ደቂቃ ላይም ሙሉቀን አዲሱ አዲስ ግደይ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምትን ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ በአግባቡ በመጠቀም አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባዎች በተወሰነ መልኩ ከጥንቃቄ አጨዋወታቸው የወጡ ቢመስልም በሂደት ግን አሉታዊ ቅያሬዎችን በማድረግ በጨዋታው ያገኙትን ውጤት ለማስጠበቅ ሲታትሩ በአንፃሩ ሀይደር ሸረፋን ቀይረው ወደ ሜዳ ያስገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጠቅጥቆ ለመከላከል ከሚሞክረውን የአዲስ አበባ ከተማን ተከላካይ በእንቅስቃሴ ለማስከፈት ተቸግረው ተስተውሏል። ነገርግን በ84ኛው ደቂቃ በአወዛጋቢ ሁኔታ የተሰጠውን የማዕዘን ምት ሱሌይማን ሀሚድ ካሻማው ኳስ መነሻነት ናትናኤል ዘለቀ ከግቡ በቅርብ ርቀት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠራት እንዲሁም መደበኛው ደቂቃ መጠናቀቂያ ላይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ የተመለሰው አዲስ ግደይ በግሩም የመልሶ ማጥቃት ባስቆጠራት ግብ ፈረሰኞቹ 3-1 ባለድል መሆን ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን ወደ 31 በማሳደግ መሪነታቸውን ሲያስቀጥሉ አዲስ አበባዎች በ14 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።