የአሠልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 1-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሠልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል።

ደረጄ ተስፋዬ – ቅዱስ ጊዮርጊስ (ምክትል አሠልጣኝ)

ስለጨዋታው…?

መጀመሪያ እንዳሰብነው አልነበረም። ልጆቹ ከማሸነፍ ጉጉትም እኛ ከሰጠናቸው ነገርም መቸኮል ነበር። የምንደልገውን ነገር ወዲያው አላገኘንም ነበር።

ስለአዲስ ግደይ የዕለቱ ብቃት…?

አዲስ በእርግጥ ረጅም ጊዜ በጉዳት ርቆ ነበር። ከዛ ተመልሶ ወደ አራት ወር አምስት ወር ሰርቷል። ከቡድኑ ጋር መቆየቱ ጥሩ ነው። ሲገባም ብዬው ነበር። ከመግባቱ በፊት እንደሚያገባ ነግሬው ነበር። ትልቅ መነሳሳት ነበረው። በጣም ልምድ ያለው ተጫዋች ነው። በጉዳት መራቁ እንጂ ከዚህ በላይ መሆን የሚችል ተጫዋች ነው።

ስለቡድኑ ቀዳሚ ፍፁም ቅጣት ምት መቺ ጉዳይ…?

አጎሮ ነው። አጋጣሚ ነው ፤ በጊዛዊነት ሀይደር ነበር መቺ። ሀይደር ተቀይሮ ስለገባ እና አጎሮን መጀመሪያ ነግረነው ስለነበር ነው።

ስለመጀመሪያው ዙር የቡድኑ አቋም…?

ጥሩ ነው። የእኛ ቡድን ረዥም ጊዜ ከዋንጫ የራቀበት ዓመት ነበር ፤ አራት ዓመት። ከዛ ውስጥ ወጥቶ ወደ አሸናፊነት መመለሱ ራሱ አንድ ነገር ነው። ቀደም ብሎ ይሄን ያጣንበት ነገር ነበር እና አሁን በተወሰነ መልኩ እያስተካከልን ቡድኑን ከዚህ የበለጠ ለማድረግ ነው ያሰብነው።


ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ያገኙትን ውጤት ስላለማስጠበቃቸው?

ይህ ኳስ ነው ያጋጥማል። ውጤት ለማስጠበቅ የምንችለውን ሞክረናል።

ከዳኝነት ጋር በተያያዘ…?

የሚመለከታቸው አካሎች ምስሉን አይተው መፍረድ ይችላሉ። ፍርዱን ለእነሱ ትቻለሁ።

በቡድኑ ውስጥ ልምድ ያለው ተጫዋች አለመኖሩ ተፅዕኖ ነበረው?

ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው። ብዙ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ያሉበት እና አንጋፋ ክለብ ነው። ለእነርሱ ክብር አለን። እኛ ደግሞ ገና ጀማሪ ነን። ስብስባችን በወጣቶች የተሞላ ነው። ልምድ ይጎለናል። ወደፊት በሁለተኛው ዙር መሟላት የሚገባውን ለማሟላት እንሞክራለን። ክፍተት ቦታዎችም ስላሉን ለማሟላት እንሞክራለን።

በቡድኑ ተጫዋቾች ውስጥ ስለሚታየው ግለኝነት?

ልጆች ስለሆኑ እና ልምድ ስለሌለ ነው። ይሄ ከልምድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። ወደፊት እያወቁ እና ልምድ እያገኙ ሲሄዱ ይቀርፋሉ።

በሁለተኛው ዙር ዝውውር ላይ ትሳተፋላችሁ?

በየቦታው ጉድለት አለ። በቦታዎቹ ላይ ገበያው ላይ ያሉትን ነገሮች እናያለን። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ለወጣቶቹ ልምድ እንዲያስተላልፉ ለማድረግ በዝውውሩ እንሳተፋለን።