ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ጅማ አባ ጅፋር

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።

የውድድር ዓመቱን በድል የጀመሩት መከላከያዎች የመጀመሪያውን ዙር ውድድር የመጨረሻ ጨዋታም በድል በማጠናቀቅ በመጠኑ ከሚያሰጋቸው ወራጅነት ለመላቀቅ፣ በደረጃ ሰንጠረዡ ከወገብ በላይ ከሚገኙ ክለቦች ጋር በነጥብ ለመቀራረብ እና እስከ 8ኛ ደረጃ የሚያስፈነጥራቸውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ተግተው እንደሚጫወቱ ይታሰባል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት አስር ሽንፈቶችን በማስተናገድ አስር ነጥቦችን ብቻ በመያዝ በወራጅ ቀጠናው እየዳከረ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በውጤት እና በእንቅስቃሴ ደረጃ እድገት ያሳየበትን የድሬዳዋ ውድድር በአዎንታዊ መልኩ በማገባደድ ለሁለተኛው ዙር ውድድር ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል በተስፋ ለመሙላት ድልን እያለመ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይታሰባል።

በርካታ ድራማዊ ክስተቶች በነበሩበት እና ቀልብን ሳቢ ከነበረው የሀዋሳ ጨዋታ አንድ ነጥብ እንኳን ያላገኙት መከላከያዎች በምርጥ ብቃታቸው ላይ ተገኝተው ካደረጓቸው ጨዋታዎች መካከል ግን አንዱን አስመልክተውን ነበር። ለወትሮ በመከላከል ቅርፅ ዘለግ ያለውን ጊዜ ሲያሳልፍ የሚታየው ቡድኑ በጨዋታው መጠነኛ ድፍረት አሳይቶ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በርካታ የግብ ዕድሎችንም በአጥጋቢ ሁኔታ ሲፈጥር ነበር። በመሬት የኳስ ቅብብል እንዲሁም ኦኩቱ ኢማኑኤልን ዒላማ ባደረጉ ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ደርሰው በድምሩ 17 ሙከራዎችን ያደረጉ ቢሆንም በመጠኑ የአፈፃፀም (አጨራረስ) ችግር ታይቶባቸው ያገኙትን የሀይል ሚዛን በግቦች ማሳጀብ አልቻሉም። ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎችም አንዱ በፍፁም ቅጣት ምት አንዱ በቁመታሙ የግብ ዘብ መሐመድ ሙንታሪ የወረደ ስህተት ተገኙ እንጂ ቡድኑ በተደራጀ ሁኔታ በፈጠራቸው ዕድሎች የተገኙ አይደለም። በተወሰነ መልኩ ቡድኑ ነገ የሚፋለመው ጅማ በሊጉ ብዙ ግቦችን ያስተናገደ ሁለተኛው ክለብ በመሆኑ እና የኋላ መስመሩ እምብዛም ያልጠነከረ መሆኑ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዳይቸገሩ ሊያደርግ እንደሚችል መናገር ይቻላል።

እንደ መከላከያ 3-2 ተረቶ ለነገው ጨዋታ እየተዘጋጀ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በራሱ የተከላካይ እና የግብ ጠባቂ ስህተቶች ሦስት ነጥብ አስረከበ እንጂ በእንቅስቃሴ ደረጃ ለትችት የሚዳርገው ብቃት አላሳየም። ከመከላከል ውጪ በሌሎቹ የጨዋታ ምዕራፎች ከወልቂጤ በመጠኑ ተሽሎ የነበረ ቢሆንም የኋላ መስመሩ ስህተት ዋጋ አስከፍሎት ከሜዳ ወጥቷል። በሀዋሳው ውድድር አይደለም ግብ ማስቆጠር የግብ ማግባት ዕድሎችን መፍጠር ተራራ ሆኖበት የከረመው የአሠልጣኝ አሸናፊ ስብስብ በውድድሩ ካስቆጠራቸው አጠቃላይ ጎሎች 80% የሚሆነውን ነገ በሚጫወትበት ድሬዳዋ ስታዲየም አስቆጥሯል። ይህ ቁጥር ቡድኑ ምን ያህል በማጥቃቱ ረገድ እንደተሻሻለ የሚጠቁም ሲሆን ዕድሎችንም ከየአቅጣጫው በመፍጠር ረገድ እድገት አሳይቷል። ይህ መሻሻል ነገም ከተነሳሽነት ጋር ታጅቦ የሚገኝ ከሆነ ደግሞ የመከላከያ ተከላካዮች ግባቸውን ላለማስደፈር የሚሰሩት ሥራ ላይ ተጨማሪ ራስ ምታት የሚሆን ይመስላል። ከወገብ በላይ ይህ መሻሻል ቢኖርም በጠቀስነው የወልቂጤ ጨዋታ ቡድኑ ላይ የታየው የመከላከል ችግር ግን እንደ ፊት መስመሩ መታደስ ይገባዋል። ግለሰባዊ የአቋቋም እና የውሳኔ ችግሮችም ተቀርፈው መምጣት አለባቸው።

በሊጉ ዝቅተኛ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠሩት መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋር ነገ በተቃራኒ የፍፁም ቅጣት ምት ስል መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን ለማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎት ሊያሳዩ ስለሚችሉ ከሳጥን ሳጥን የማያቋርጥ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሊፈጠር ይችላል። በተለይ ሁለቱም ወደመሐል ሜዳው ገፋ ብለው ሊከላከሉ ስለሚችሉ ፈጣኖቹ አጥቂዎቻቸው ከተከላካይ ጀርባ እየተገኙ አደጋ መፍጠራቸው አይቀርም። በዋናነት ደግሞ በመከላከያ በኩል የቡድኑ የልብ ምት ቢኒያም በላይ ለጅማ ተከላካዮች የሜዳ ላይ ፈተናን ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ በጅማም በኩል በጥሩ መግባቦት ላይ የሚገኙት መሐመድኑር እና እዮብ ጥምረት ለጦሩ ችግር ሊሆኑ ይችላሉ።

በምንገኝበት የጨዋታ ሳምንት በርካታ ክለቦች ጓዳ የኮቪድ-19 ኬዞች ቢበረክቱም መከላከያ እና ጅማ ቤት በድምሩ አንድ ኬዝ ብቻ መኖሩ ተገልጿል። ከሀዋሳ ውድድር ጀምሮ አንድም የኮቪድ ኬዝ ያልተመዘገበበት መከላከያ በዚህም ሳምንት ነፃ ሲሆን ጅማ ግን አንድ ተጫዋች በቫይረሱ ያጣል። ከዚህ ውጪ ሁለቱም ጋር ጉዳት እና ቅጣት እንደሌለም ተመላክቷል።

10 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ተፈሪ አለባቸው በመሐል አልቢትርነህ ፋሲካ የኃላሸት እና ወጋየሁ አየለ በረዳት ቴዎድሮስ ምትኩ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው ጅማ አባ ጅፋር 3 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መከላከያ እስካሁን ጅማን አሸንፎ አያውቅም። በግንኙነታቸው ጅማ 7 በማስቆጠር የበላይ ሲሆን መከላከያ 1 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ማሞ

ግሩም ሀጎስ – ኢማኑኤል ላርዬ – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ

ኦኩቱ ኢማኑኤል – ተሾመ በላቸው

ጅማ አባጅፋር (4-3-3)

አላዛር ማርቆስ

በላይ አባይነህ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድማገኝ ማርቆስ

ዳዊት እስቲፋኖስ – አዛህሪ አልመሃዲ – መስዑድ መሐመድ

ዳዊት ፍቃዱ – መሐመድኑር ናስር – እዮብ አለማየሁ