ሳላዲን ሰኢድ ከአልጄርያው ጨዋታ ውጭ ሆነ

በጉዳት እና ከምርጫ በመዘለሉ ምክንያት ከብሄራዊ ቡድን ርቆ የቆየው ሳላዲን ሰኢድ ኢትዮጵያ ከአልጄርያ ጋር ለምታደርጋቸው ጨዋታዎች በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጥሪ ቢደረግለትም መጫወት እንደማይችል ሪፖርት በማድረጉ ከብሄራዊ ቡድን ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በቅርቡ ቅዱስ ጊየርጊስን በአጭር ጊዜ ውል የተቀላቀለው ሳላዲን ሰኢድ ባለፈው ሳምንት ከተጠሩ 24 ተጫዋች ዝርዝር ውስጥ ቢካተትም አንድም ቀን ልምምድ ሳይሰራ ቀርቷል፡፡

2008 የውድደረር ዘመንን ‹‹መርሳት የምፈልገው የውድድር ዘመን›› እንደሆነ ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ የተናገረው ሳላ በውድድር አመቱ በቂ የውድድር ጨዋታዎችን ማድረግ ባለመቻሉ በአእምሮ እና በአካል ረገድ ለጨዋታ ያለው ዝግጁነት ብቁ ደረጃ ላይ እንደማይኝ በማመኑ ከአልጄርያ ጋር የሚደረጉት ጨዋታዎች ላይመሰለፍ እንደማይችል ለአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በማሳወቅ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጪ ሆኗል፡፡ በጉዳዩ ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን አስቴየት ለማካተት ጥረት ብታደርግም በአልጄርያው ጨዋታ እና በተጫዋች ጉዳቶች ዙርያ ጠቅላላ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰኞው የአልጄርያ ጉዟቸው በፊት እንደሚጠሩ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአሁኑ ሰአት በሁነኛ አጥቂ እጥረት ላይ ይገኛል፡፡ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢነትን የሚመራው ታፈሰ ተስፋዬ በጉዳት ከአልጄርያው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ የመከላከያው ሙሉአለም ጥላሁንም በጉዳት እስካሁን ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ልምምዶች መስራት አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ሳላዲን ሰኢድ ከቡድኑ ውጪ በመሆኑ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በአጥቂ መስመራቸው ላይ በ2005 የውድድር ዘመን በደደቢት ማልያ በጋራ 43 ግቦች ከመረብ ያሳረፉት ዳዊት ፍቃዱ እና ጌታነህ ከበደ ላይ ብቻ እምነታቸውን ለመጣል ይገደዳሉ፡፡ በተያያዘ ዜና የብሄራዊ ቡድኑ አምበል ስዩም ተስፋዬ ትላንት በልምምድ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ኣቋርጦ የወጣ ሲሆን በዛሬው ልምምድ ላይም የቡድኑን ልምምድ ተቀምጦ ለመመልከት ተገዷል፡፡ ጉዳቱ መጠነኛ እንደሆነ ቢገለፅም ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት በቢልዳ ከተማ ለሚደረገው ጨዋታ የመድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *