ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የውድድሩን መጋመስ በሚያበስረው የነገ ምሽቱ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች አንስተናል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለው የነበሩት የነገዎቹ ተጋጣሚዎች ድሬዳዋን በተከታታይ ድል ለመሰናበት ይፋለማሉ። ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ በጥሩ መነቃቃት ሁለት ጨዋታዎችን ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች አራት ነጥቦችን አሳክተው በሰንጠረዡ አጋማሽ ሲቀመጡ እስከ ስድስተኛነት ከፍ የማለት ዕድል ይኖራቸዋል። በድሬዳዋ ቆይታው ዘጠኝ ነጥቦችን የሰበሰበው ወላይታ ድቻ ደግሞ የውድድሩን አጋማሽ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ደረጃ ላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ ነገ ወደ ሜዳ ይገባል።

ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና መምጣት በኋላ በሜዳ ላይ መተግበር የሚያስበው ዕቅድ ፍንጭ እየታየ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ነገ ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች የተለየ ተጋጣሚን ያገኛል። ኳስን በቶሎ መልሶ መንጠቅ እና በቅብንሎች ላይ ተመስርቶ በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚያስበው ቡድኑ ጥርት ያለ ገፅታ በሲዳማው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ነበር የታየው። የጅማው ድል ውጤት ከማሳካት አንፃር በጎ ቢሆንም ይህንን የጨዋታ ዕቅድ በወጥነት በመተግበሩ በኩል ግን የተቀዛቀዘ ነበር። በተለይም በሁለቱም ጨዋታዎች ሁለተኛ አጋማሾች እየወረደ የሚታየው የቡድኑ ጠጣርነት እና ጨዋታን በራሱ መንገድ የማስኬድ አቅም ሙሉ ደቂቃውን በተመሳሳይ አካላዊ ብርታት እና የመከላከል ትኩረት ከሚያሳልፉት ወላይታ ድቻዎች አንፃር ችግር ላይ ሊጥለው ይችላል። የዚህን ምልክት ደግሞ የቡድኑ ደካማ ጎን ሆኖ የሰነበተው ሰዒድ ሀብታሙ ብቃት በመታገዝ ነጥብ ይዞ የወጣባቸው የጅማ ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃዎች አሳይተውን አልፈዋል።

ወልቂጤ ከተማ አመዛኙን ደቂቃ በተጋጣሚው አጋማሽ እንደሚያሳልፍ በሚጠበቅበት የነገው ጨዋታ ከላይ የተጠቆመው የቡድኑ አጨዋወት በጥሩ አተገባበር መታየት ይኖርበታል። በተለይም ክፍተት ላለመስጠት በትኩረት ከሚጫወተው ታታሪው ተጋጣሚው አንፃር በሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግቢያ ላይ በማጥቃት ወቅት የሚኖረው ስብጥር እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ወደ መሀል አጥብበው ከሚንቀሳቀሱ አማካዮቹ እንዲሁም ወደ ኋላ ተስበው ቅብብሎችን ከሚከውኑ አጥቂዎቹ ውጪ ሰፋ የሚለውን ኮሪደር በሙሉ አቅም ለመጠቀም የሚጥሩት የመስመር ተከላካዮቹ የነገ ብቃት ጨዋታውን የመወሰን አቅም ይኖረዋል። በዚህ ረገድ የተጋጣሚን ስህተት በቶሎ መጠቀምን ጨምሮ በተከታታይ የታይበትን የግብ ማግባት ችግር በጅማው ጨዋታ ቀርፎ ለነገ መድረሱ ለቡድኑ አቅም ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ሲታሰብ ግለሰባዊ ስህተቶችን መቀነስ እና ለመልሶ ማጥቃት አለመጋለጥ ደግሞ ተጨማሪ የቤት ሥራዎቹ ናቸው።

ወላይታ ድቻ እንደቡድን ያለውን ጥንካሬ ከጨዋታ ዕቅዱ ጋር በአግባቡ እያጣጣመ ራሱን በሚገልፅ አቀራረብ ነጥቦችን መስብሰቡን ቀጥሏል። በቀላሉ ግብ ከማያስተናግዱ ቡድኖች መካከል የሆነው ወላይታ ድቻ የመከላከል ቅርፁን በቶሎ በመያዝ አይታማም። ወደ ሽግግር ከመግባቱ በፊትም የመከላከል አቋቋሙን ጠብቆ ክፍተት ሳይሰጥ የሚቆይበት ሁኔታ በተለይም የኳስ ቁጥጥርን ለሚያዘወትሩ ቡድኖች በቀላሉ እንዳይሰበር ምክንያት እየሆነው ይገኛል። ሆኖም ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የተጋጣሚን ጀርባ አደገኛ በሆኑ ረዘም ያሉ ኳሶች የሚያጠቃባቸው አጋጣሚዎች መመናመን እየታየባቸው ይገኛል። ሀዲያ ሆሳዕናን በአንድ ግብ ልዩነት እንደረታበት ጨዋታ የተጋጣሚን ስህተት ወደ ግብ የመቀየር ስኬቱ ጥሩ መሆን ካልቻለ በራሱ መንገድ ወደ ግብ ደጋግሞ የሚደርስበት ሂደት መዳከም ነገም ከግብ ሊያርቀው እንደሚችል ይታሰባል።

የጦና ንቦቹ በመከላከል ዕቅዳቸው ውስጥ የተጋጣሚን ዋና የማጥቃት መስመሮች መዝጋት ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ይታያል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ነገም በግራ እና ቀኝ በኩል በሜዳው ቁመት ጣንካራ ጥምረትን በመፍጠር የወልቂጤን የክንፍ እንቅስቃሴዎች ለመዝጋት እንደሚጫወቱ ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር የሰራተኞቹ ሁለቱም የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ደመ ነፍስ ያላቸው መሆኑ የወላይታ ድቻን የሽግግሮች ትኩረት የሚፈትሽ ይሆናል። መሀል ለመሀልም ቢሆን ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማቸው የተጋጣሚዎቹን አማካዮች ቅብብሎች ወደ ሳጥኑ እንዳይገባ ለማድረግ የሚጠቀመው የአማካዮች ጥምረት በጨዋታው ከባባድ ፍልሚያዎችን ሊያስመለክተትን ይችላል። ያም ሆኖ ግን ወላይታ ድቻ የመልሶ ማጥቃት አደገኝነቱን መልሶ ማግኘት ካልቻለ ከኳስ ጋር ነፃነት የሚኖረው የወልቂጤ ከተማ የማጥቃት ድግግሞሽ ይበልጥ አደገኛ መሆኑ የሚቀር አይመስልም።

ወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኙን በኮቪድ ምክንያት ከማጣቱ በቀር ሌላው ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑን ስንሰማ በኃይሉ ተሻገርን በቅጣት ምክንያት በማያገኘው ወልቂጤ ከተማ በኩልም ሁለት የኮቩድ ኬዞች መኖራቸው ታውቋል።

ጨዋታውን ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት ሸዋንግዛው ተባበል እና አበራ አብርደው በረዳትነት ሊዲያ ታፈሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በአምናው የሊጉ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች በቅድሚያ ወልቂጤ ከተማ 2-1 ሲርታ በቀጣይ 1-1 ተለያይየዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

አህመድ ሁሴን – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

ወላይታ ድቻ (4-4-2)

ወንድወሰን አሸናፊ

በረከት ወልደዮሐንስ – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

ያሬድ ዳዊት – አዲስ ህንፃ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ

ስንታየሁ መንግሥቱ – ምንይሉ ወንድሙ