[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ቀዝቃዛ ፉክክር በተደረገበት ፍልሚያ መከላከያ እና ጅማ አባ ጅፋር ያለ ግብ ተለያይተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በክስተቶች በተሞላው መርሐ-ግብር በሀዋሳ ከተማ 3-2 የተሸነፉት መከላከያዎች በዛሬው ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አዲሱ አቱላ፣ ገናናው ረጋሳ እና ቢኒያም በላይን በአቤል ነጋሽ፣ ቢኒያም ላንቃሞ እና ኢብራሂም ሁሴም ለውጠዋል። በተመሳሳይ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የ3-2 ሽንፈት በወልቂጤ ከተማ ያስተናገዱት ጅማ አባ ጅፋሮች በበኩላቸው ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በለውጦቹም አድናን ረሻድ እና ዳዊት ፍቃዱ የአዛህሪ አልመሀዲ እና በላይ አባይነህን ቦታ ተክተው ወደ ሜዳ እንዲገቡ ተደርጓል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በዛሬው ዕለት በድምቀት እየተከበረ የሚገኘው 126ኛው የአድዋን የድል በዓል ታስቧል። የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ከሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ጋር በመሆን የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ሲሆን በማርሽ ባንድ ታጅበውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ዘምረው ጨዋታውን አስጀምረዋል።
ጥንቃቄ ላይ ያተኮረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀልብን የሚገዛ ሆኖ አልተገኘም። በእንቅስቃሴ ደረጃ መከላከያ በረጃጅም ኳሶች ወደ ጅማ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞልርም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር አልቻለም። ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ኳስ ቁጥጥር ላይ ጥሩ ቢሆንም የመከላከያን የኋላ መስመር ሰብሮ መግባት ሳይችል ቀርቷል። ግማሽ ሰዓት ካለፈ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ፈጥረው ተመልሰዋል። በዚህም ከግራ ማዕዘን አካባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ ለመስዑድ መሐመድ አቀብሎት መስዑድ የመታው ኳስ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቷል። በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው በቀዝቃዛነቱ ዘልቆ ያለ ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አጋማሹ ተገባዷል።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደ መጀመሪያው ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ አልቀጠለም። የመጀመሪያውን አጋማሽ ብቸኛ ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉት ጅማዎችም በ49ኛው ደቂቃ ሌላ ጥቃት ሰንዝረው የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት ተስተናግዷ። በዚህም ዳዊት እስጠፋኖስ በቀጥታ የሞከረውን የቅጣት ምት ኳስ ክሌመንት ቦዬ እንደምንም ባያወጣው ኳስ እና መረብ ሊገናኙ ነበር።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መጠነኛ መነቃቃት ያሳዩት ሁለቱ ቡድኖች ጎሏቸው የነበረውን የማጥቃት ፍላጎት ለማግኘት ሲጣጣሩ ነበር። መከላከያም በ53ኛው ደቂቃ በረጅሙ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ግሩም ሀጎስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ባይወጣበት መሪ ሊሆኑ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግሩም በድጋሚ ከመስመር አምልጦ በመውጣት አደጋ ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ በአላዛር ጥረት መክኖበታል። የቆሙ ኳሶችን እንደ ዋነኛ የግብ ምንጭነት መጠቀም የያዙት ጅማዎች በድጋሚ ከቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ቀዳሚ ሊያረጋቸው ቢጥርም ጠንካራውን ሙከራ ክሌመንት አውጥቶበታል።
በ82ኛው ደቂቃ መከላከያ እጅግ አስቆጪ ዕድል አምክኗል። በዚህም ኦኩቱ ኢማኑኤል ከርቀት የተላከለትን ጥሩ ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ለግቡ በምርጥ አቋቋም ላይ ቢገኝም ኃይል አብዝቶ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። እንደ መጀመሪያው ደቂቃዎች የጨዋታው መገባደጃም ግብ ጠባቂዎች ሳይፈተኑበት ቀርቶ ቡድኖቹ ጨዋታውን ሲጀምሩ የነበራቸውን 1 ነጥብ ከሜዳ ይዘው ወተዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ግን የአብስራ ሙሉጌታ በብሩክ ሰሙ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ከሜዳው ተወግዷል።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 18 በማድረስ አንድ ደረጃ በማሻሻል 11ኛ ደረጃን ሲይዝ ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በ11 ነጥቦች ያለበት 15ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።