[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
እጅግ የወረደ ፉክክር ካስመለከተው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።
ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ስለ ውጤቱ?
ከተጫወትነው ጨዋታ አንፃር እኩል ለእኩል በቂ ነው። እኛም እነሱም ተመልካችን የሚያስደስት ጨዋታ ተጫውተናል ብዬ መናገር አልችልም። ውድድሩን ለመጨረስ የተደረገ ነገር ነው የሚመስለው። ይሄን ያህል አደገኛ ኳሶች እና ደጋፊን የሚያስጨፍር ነገር በእኛም ሆነ በእነርሱ በኩል ብዙ የታየ ነገር የለም። በቃ ለመጨረስ የተደረገ ጨዋታ ነው የሚመስለው።
እንቅስቃሴው ቀዝቀዝ ስላለበት ምክንያት?
እኛ ጋር የተጫዋቾች መጉደል አለ። የቢኒያም፣ አዲሱ እና ገናናው አለመኖር። አሁንም የምናስገባቸው ወጣቶች ናቸው። ግን ዕድሉም መጠቀም ካልቻሉ በወጣትነት ብቻ አይሆንም። ዕድሉን መጠቀም መቻል አለብህ። ተቀምጠው የነበሩ ተጫዋቾች መጫወት ሲጀምሩ የጨዋታ የአካል ብቃት የሚባሉ ነገሮች እየወረዱ ይመጣሉ። ለዚህም ነው በ45 ደቂቃ የቀየርነው። ምክንያቱም የጨዋታ የአካል ብቃት ላይ ካልሆንክ እንደዚህ ሙቀት ውድድር ላይ ቶሎ ትደክማለህ።
አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር
ጨዋታው እንዴት ነበር?
ጥሩ የመሸናነፍ ትግል የተደረገበት ጨዋታ ነው። ማሸነፍ በጣም እንፈልግ ነበር። አንድ ከምንም ስለሚሻል ተመስገን ነው።
በሁለተኛው አጋማሽ ያገኟቸውን ዕድሎች ስላለመጠቀማቸው?
ተጫዋቾቼ ላይ መጓጓት አለ። አሸንፎ ለመውጣት የነበራቸው ተነሳሽነት በጣም ከፍተኛ ነው። መከላከያ ደግሞ ሲከላከል የመደራጀት አቅሙ በሀገራችን ውስጥ ካሉ ምርጥ የመከላከል አቅም ካላቸው እና ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ሆነው ከሚጫወቱት አንዱ ነው። ትንሽ ጎል ከገባባቸው ቡድኖች መደዳም ይገኛል። መጫወቻ ሜዳዎችን አሳጥቶናል። ተንደርድረን ለማጥቃት ያሰብናቸውን ነገሮች ዘግተውብናል። ዞሮ ዞሮ ለማሸነፍ የነበረን ትግል ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።
ሁለተኛውን ዙር ስለሚቀርቡበት መንገድ?
ተጫዋቾችን ብናገኝ በጣም ደስ ይለኛል። ግን ጥሩ ተጫዋች ማን ይለቃል ሌላው ፈተና ነው። ይሄ ሁሉ ዋጋ ያስከፈለም መጀመሪያ አመላመል ላይ ነው። ያ ባይበላሽብን ኖሮ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ በፍፁም እንገኛለን ብዬ አላስብም። ሁለተኛው ዙር ላይ ከተሳካልን ሁለት ሦስት ተጫዋች ማምጣት የውዴታ ግዴታ ይሆናል።