የኢትዮጵያ ከ20 በታች ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት የዛሬ ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ ጎንደር ላይ የተደረጉት የምድብ ሀ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና 0-0 አርባምንጭ ከተማ

ሁለቱ ቡድኖች ተመሳሳይ መለያ ለብሰው ወደ ሜዳ በመምጣታቸው ምክንያት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማዎች የተሻለ የግብ ሙከራ ያደረጉበት ቢሆንም ቡድኑ ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። በአጠቃላይ እንደውም በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የረባ የግብ ሙከራ ሳይደረግበት ቀርቷል። በሁለተኛው አጋማሽም አርባምንጮች ወደግብ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ቢያሳዩም ውጥናቸው አልሰመረም። ጨዋታውን 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


አዳማ ከተማ 1-1 ሰበታ ከተማ

8:00 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማን ከሰበታ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተፈፅሟል። በመጀመሪያው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ የተለያየው አዳማ ፍፁም ተሻሽሎ የመጣበት ጨዋታ ነበር። መሐል ሜዳ ላይ የተሻለ የነበረው ቡድኑም ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያስመለክትም ሰበታዎች ጥሩ የመከላከል ብቃት አሳይተው ግብ ሳይቆጠር ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ በጥሩ የጨዋታ ሂደት ወደ ሰበታ ግብ ክልል የሄደውን ኳስ ግብ ጠበቂው ከቀኝ መስመር ሲሻማ ይዞ በመልቀቁ ኢብራሂም አብዱላዚዝ አግኝቶት ወደ ግብ ቀይሮ አዳማ መሪ ሆኗል። በድጋሜ 61ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማው የመስመር አጥቂ አብዱልፈታህ ሰፊ ግብ ጠብቂውን አልፎ ወደ ግብ የመታው ኳስ ሌላ ግብ ሊሆን የተቃረበ አጋጣሚ ነበር።

ሰበታ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በ89ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው አጋጣሚውንም ኤርሚያስ አበራ ወደ ግብነት ቀይሮት አቻ ሆነዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።


ሲዳማ ቡና 1-1 ሀላባ ከተማ

10:00 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና እና ሀላባ ከተማን ያገናኘው ጨዋታም በተመሳሳይ 1-1 ተጠናቋል። አዝናኝ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የተገኙ ሦስት ፍፁም ቅጣት ምቶች የተሳቱበት እና ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ገና በ5ኛው ደቂቃ የሀላባ ከተማ የመሐል ተከላካይ አሸናፊ ሀብቴ ከቀኝ መስመር የተሻማ ኳስ አወጣለው ሲል ተቆርጦበት እራሱ ላይ አግብቶ ጨዋታውን ሲዳማዎች መምራት የጀመሩ ሲሆን ከአራት ደቂቃ በኋላ ደግሞ በእጅ ከተነካ ኳስ የተገኘ የፍፁም ቅጣት የሀላባ ከተማው አቢቲ ሮባ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በተጨማሪም ዳመና ደምሴ ሳጥን ውስጥ ወደ ግብ በቀጥታ አክርሮ የመታው ኳስ የግብ ቋሚ የመለሰበት ሌላ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። በድጋሜ 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡና ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በፍቅሩ ግዛቸው ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከአራት ደቂቃ በኋላ ሀላባዎች በድጋሜ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው አብዱልአዚዝ አብደላ አምክኖታል። 37ኛው ደቂቃ ላይ ታምራት አበራ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ግብ ቀይሮ አቻ ሆነው ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ ግን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራዎች ሳይኖር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተገባዷል።