የአርቢትር አዳነ ወርቁ ወቅታዊ ሁኔታ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ15ኛው የሊጉ ሳምንት በተመደቡበት ጨዋታ ላይ ሳሉ ጉዳት ካስተናገዱት የመሀል ዳኛ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ሲከናወኑ የቆዩት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ ተቋጭተዋል። በመጨረሻው ሳምንት በነበሩ የሊጉ አጋማሽ ጨዋታዎች ላይ ከተከሰቱ አጋጣሚዎች ውስጥ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሲዳማ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕናን ባገናኘው ጨዋታ የመሀል ዳኛው አዳነ ወርቁ ጉዳት አስተናግደው ከሜዳ መውጣታቸው አንዱ ነበር። ጨዋታው 10ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ያኩቡ መሀመድ ከባዬ ገዛኸኝ ኳስ ለማስጣል ባደረገው ጥረት ሳይታሰብ ግጭት ያደረሰባቸው አርቢትሩ አራተኛ ዳኛ በነበሩት ተከተል ተሾመ ተተክተው ከሜዳ በመውጣት የመጀመሪያ ዕርዳታ ሲደረገላቸው በዛው በድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ህክምናም አግኝተዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ አርቢትሩ ስላሉበት ሁኔታ ለማጣራት ባደረገችው ጥረት ከዚህ ቀደም በዳኝነት ዘመናቸው መሰል አጋጣሚ ተፈጥሮባቸው እንደማያውቅ የገለፁት ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አሳውቀዋል። በወቅቱ ከቁርጭምጭሚታቸው ከፍ ብሎ ባለው ቦታ ላይ ከበድ ያለ ግጭት አስተናግደው እንደነበር በማስታወስ በጊዜው ባገኙት የመጀመሪያ ዕርዳት በረዶ ተደርጎላቸው የማስታገሻ መረፌ መወጋታቸውን ተናግረዋል። በመቀጠል ድሬዳዋ በሚገኘው የማሪያምወርቅ ሆስፒታል ኤክስሬይ የተነሱ ሲሆን በዉጤቱም ከቅጥቅጥ ባለፈ ከባድ የሚባል ጉዳት እንዳልገጠማቸው ታውቋል። አርቢትሩ ህክምናቸውን ተከታትለው ከሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ትናንት ከድሬዳዋ የወጡ መሆኑን እና ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ልምምድ እንደሚመለሱ ጨምረው ገልፀውልናል።