የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ15ኛ የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾችን በዚህኛው ፅሁፋችን ለመዳሰስ ሞክረናል።

👉 ለአዲስ ግደይ የማይረሳው ምሽት

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መጋቢት 3 ላይ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በ72ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴን ተክቶ ወደ ሜዳ በመግባት በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታውን ያደረገው አዲስ ግደይ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቡድኑ ከቀድሞ ክለቡ ሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ የጉልበት ጉዳት ማስተናገዱ አይዘነጋም።

በዚህ ምክንያት የጉልበት ቀዶ ጥገና ያደረገው ተጫዋቹ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ከጉዳቱ አገግሞ ቀለል ያሉ ልምምዶችን እየሰራ ከፈረሰኞቹ ስብስብ ጋር ቆይታ ቢያደርግም በሜዳ ላይ ሳንመለከተው ቆይተናል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን በርካታ ቀዳሚ ተሰላፊዎቹን በኮቪድ ምክንያት ማግኘት ያልቻለው ቡድኑ አዲስ ግደይ አንድ ዓመት ከተጠጋ ጊዜ በኋላ ዳግም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ወደ ሜዳ እንዲገባ አድርጓል።

በጨዋታው ከረጅም ጊዜ ከጉዳት እንደተመለሰ ተጫዋች ከጨዋታ ዝግጁነት ጋር በተያያዘ ብዙ እንደሚቀረው በሚያሳይ መልኩ ቀዝቃዛ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያሳለፈው አዲስ ቡድኑ ወደ አቻነት የመጣበት የፍፁም ቅጣት ምት እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። በመቀጠል መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ላይ በድንቅ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከሀይደር ሸረፋ የደረሰውን ኳስ ከአዲስ አበባ ተከላካዮች አምልጦ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን አሸናፊነት ያረጋገጠች ሦስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ይህችም ግብ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ድሬዳዋ ከተማ ላይ በመጀመሪያው ዙር ካስቆጠራት ግብ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ያስመዘገባት ሁለተኛ ግብ ሆና የተመዘገበች ሲሆን ከዚህም በላይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት ለተመለሰው ተጫዋች የእግርኳስ ህይወት ትልቅ ትርጉም የሚኖራት ግብ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያለው ውል የሚጠናቀቀው ተጫዋቹ የጨዋታ ዝግጁነቱን በፍጥነት በማግኘት ለዋንጫ እየተፎካከረ የሚገኘውን ቡድኑን ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ የነበረው አዲስ በጣም ከባድ ጊዜ ስለማሳለፉ ገልፆ አሁን ላይ በጤንነትም ሆነ በተነሳሽነት ረገድ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ግቧንም ለክለቡ ደጋፊዎች መታሰቢያ እንደሚያደርግ ተናግሯል።


👉 ሽመክት ጉግሳ ተመልሷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ፋሲል ከነማ የሊጉ አሸናፊ ሲሆን እጅግ የላቀ አበርክቶ የነበረው ሽመክት ጉግሳ ዘንድሮ ግን የአምናውን የውድድር ዘመን ብቃቱን ሜዳ ላይ ለመድገም ተቸግሮ ቆይቷል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አስራ አንድ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በሊጉ ቀዳሚ የነበረው ሽመክት ዘንድሮ ግን እጅግ የተቀዛቀዘ ተሳትፎን እያደረገ ይገኛል። ከዚህ የጨዋታ ሳምንት በፊት በነበሩ 14 የጨዋታ ሳምንታት በአስራ ሦስቱ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ተጫዋቹ ለ1126 የጨዋታ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ተሳትፎ የነበረው ሲሆን በዚህም ምንም ግብ ሳያስቆጥር ሁለት ኳሶችን ብቻ ለግብ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ይህም ከአምናው አንፃር ቢያንስ በጨዋታ ተሳትፎ (out put) ረገድ ምን ያህል ደካማ ጊዜ እያሳለፈ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።

ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን 4-0 ሲረታ ግን ተጫዋቹ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ በረከት ደስታ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ያስቆጠረው ሽመክት በሁለተኛው አጋማሽም ከዓለምብርሃን ይግዛው የደረሰውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ከመረብ በማገናኘት ቡድኑን ለድል አብቅቷል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የመጨረሻ ግቡን በ22ኛ የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን ወልቂጤን 1-0 ሲረታ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠር ያስመዘገበው ሽመክት ከ10 ወራት በኋላ ዳግም ከግብ ታርቋል። ከግቦቹ በኋላ ያሳያቸው በስሜት የተሞሉ የደስታ አገላለፆች ተጫዋቹ የነበረበትን አዕምሮአዊ ጫና በግልፅ የሚያመላክቱ ሲሆን ግቦቹ ከዚህ ሂደት ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖራቸውም ይጠበቃል።

እንደ ቡድን ባለፉት ዓመታት ፋሲል ከነማን በወጥነት ሲያገልግሉ የነበሩት ወሳኝ ተጫዋቾች በጥቅሉ ዘንድሮ በአቋማቸው ወረደው እየተመለከትን የምንገኝ ሲሆን የሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ አግቢነት እና ወደ ቀደመው ብቃቱ የመመለስ ፍንጭ መስጠቱ በተለይ ፋሲል ከነማ በሁለተኛው ዙር ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ሁለገቡ አሥራት ቱንጆ

በአሁናዊ የእግርኳሳችን ሁኔታ ስለሁለገብ ተጫዋቾች ስናስብ በቀዳሚነት ወደ አዕምሯችንን ከሚመጡ ስሞች መካከል አስራቱ ቱንጆ አንዱ ነው።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን እንኳን አስራት ለኢትዮጵያ ቡና በቀኝ እና በግራ መስመር ተከላካይነት ፣ በመስመር አጥቂነት እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በመሀል አማካይነት ቡድኑን ሲያገለግል ተመልከተነዋል።

ጅማ አባ ጅፋርን ለቆ በ2009 የክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለ ወዲህ ቡድኑ በፈለገው ቦታ ያለውን ሳይሰስት እየሰጠ የሚገኘው አስራት በተሰለፈባቸው የመጫወቻ ቦታዎች ሁሉ ጥሩ ጥረቶችን ሲያደርግ እየተመለከትነው እንገኛለን።

በትልቅ ደረጃ በሚገኝ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ተቀዳሚ ፍላጎታቸው የጨዋታ ደቂቃ የማግኘት ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ ባለፈ ግን ምቾት በሚሰጣቸው የመጫወቻ ቦታ ላይ የመጫወታቸው ጉዳይ አቅማቸውን ይበልጥ እንዲያወጡ ሊረዳቸው ይችላል። ሁለገብ ተጫዋች በመሆን ውስጥ ግን ይህ ተደጋጋሚ የሚና ለውጥ በግል የእግርኳስ ህይወት ዕድገት ተጫዋቾችን በአንድ መጫወቻ ቦታ ላይ ልቀው እንዳይወጡ ከማድረግ አንፃር በሚፈጥረው ተግዳሮት ለተጫዋቾች ጉዳት ሊኖረው እንደሚችልም በተለያዩ ተጫዋቾች የተመለከትነው እውነታ ነው። ከዚህ አንፃር አስራት በክለቡ የጨዋታ ጊዜን በወጥነት እያገኘ በብሔራዊ ቡድንም የመመረጥ አጋጣሚ የተፈጠረለት ሲሆን ሂደቱ በግል የእግርኳስ ህይወቱ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ወደ ፊት የምንመለከተው ይሆናል።

👉 ደምቆ ያመሸው ሮቤል ተክለሚካኤል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ የዝውውር መስኮት ቀይ ባህርን ለቆ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ኤርትራዊው አማካይ በዘንድሮ የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ቡና አማካይ መስመር የሌለውን የተለየ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝ ካሳዬ 4-3-3 ውስጥ ከሁለቱ ስምንት ቁጥሮች አንዱ በመሆን ከሳጥን ሳጥን በተለየ ብርታት በማጥቃት እና በመከላከል ጥሩ አቅሙን ሲያሳይ የቆየው አማካዩ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አማኑኤል ዮሀንስ በአምስት ቢጫ መሰለፍ አለመቻሉን ተከትሎ በስድስት ቁጥር ሚና ጨዋታውን በመጀመር አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል።

ለወትሮው በጫና ውስጥ ኳሶችን ለመመስረት ሲቸገር ለምናስተውለው ኢትዮጵያ ቡና ሮቤል በጫና ውስጥ እንኳን ሆኖ የመጀመሪያውን የምስረታ ሂደት በማሳለጥ ረገድ የነበረው አፈፃፀም አስደናቂ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ደግሞ የረጃጅም ኳሶች ስርጭቱም እንዲሁ ግሩም ሆኖ አምሽቷል።

አንድ ለአንድ በተጠናቀቀው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአቡበከር ናስር አማካኝነት ላስቆጠሯት ግብ መነሻ የሆነችውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመሀል ሜዳ ያደረሰው ሮቤል በአጋማሹ የተመጠኑ ረጃጅም ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በመላክ በቅብብል ተጋጣሚ ሳጥን ላይ ለማድረስ ተቸግሮ ለነበረው ቡድኑ አማራጭ ምላሽን ይዞ ቀርቧል።

ተቀራራቢ ዓይነት የጨዋታ ባህሪ ባላቸው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ለተሞላው የካሳዬ አራጌው ስብስብ እንደ ሮቤል ያሉ በተወሰነ መልኩ የጨዋታ ባህሪያቸው የተለዩ አማካዮች መኖራቸው ለቡድኑ የሚሰጠውን ጠቀሜታ የባህር ዳሩ ጨዋታ በግልፅ ያስመለከተ ነበር።

👉 ለብዙ ታዳጊዎች ተስፋን የሚፈነጥቀው ሻሂዱ መስጠፋ

በዘመናት መካከል በዝቅተኛ ደረጃ እየዳከረ የሚገኘው እግርኳሳችንን ለመቀየር በመፍትሔነት ከሚቀርቡ ጉዳዮች አንዱ በታዳጊ እና ወጣት ተጫዋቾች ላይ መጠነ ሰፊ ስራዎችን መስራት እንደሆነ በስፋት ይነገራል።

ታድያ ይህንን በስፋት የሚሰነዘር ሀሳብ ወደ መሬት ለማውረድ በክለብ ጥላ ስር ከሚሰሩ ስራዎች በተጨማሪ ውስን የሆኑ በግለሰቦች የሚተዳደሩ የታዳጊዎች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ወደ ተግባር ገብተው እየተመለከትን እንገኛለን። ከእነዚህ መካከል በአሰልጣኝ አብይ ካሳሁን መስራችነት ወደ ስልጠና የገባው “ሀሌታ የታዳጊዎች የእግርኳስ ስልጠና ማዕከል” አንዱ ነው።

ማዕከሉ ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት አንስቶ ያሉ ህፃናት እና ታዳጊዎችን ከዚህ ቀደም በወንዶች እና በሴቶች እግርኳስ በትልቅ ደረጃ ተጫውተው ባሳለፉ ወጣት አሰልጣኞች ስር እንዲሰልጥኑ በማድረጉ በሁለንተናዊ መንገድ የተሻሉ እግርኳሰኞችን ለማፍራት ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ታዳጊ ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚያሳዩበትን ዕድል በመፍጠር በተለያዩ የክለብ መለማዮች ዓይን ውስጥ እንዲገቡ በማገዝ ወደ ክለቦች የዕድሜ እርከን ቡድኖች እንዲበቁ ሲሰራ ቆይቷል። በማሰልጠኛ ማዕከሉ የእስካሁኑ የስልጠና ታሪክ ትልቁን ፍሬያቸውንም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በትልቁ የሀገሪቱ ውድድር ላይ ተመልክተዋል።

በ2012 በአሁኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ መልማይነት ከሀሌታ የቅዱስ ጊዮርጊስን የዕድሜ እርከን ቡድን የተቀላቀለው ሻሂዱ መስጠፋ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ሲያደርግ ተመልክተነዋል። በሊጉ ደግሞ በኮቪድ ምክንያት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መሰለፍ ባልቻሉበት እና በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸናፊነት በተጠናቀቀው የአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት ችሏል።

ይህ አጋጣሚ ለሀሌታ የታዳጊዎች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የግል የእግርኳስ ማሰልጠኛ ተቋማት ሳይቀር ታላቅ የምስራች ሆኖ አልፏል። በቀጣይም በርካታ ተጫዋቾቾ በእነ ሻሂዱ ሙስጠፋ መንገድ በሊጉ ክለቦች ዋና ቡድኖች ላይ እንደምንመለከት ተስፋ እንድናደርግ የሚያደርግ ሁነትም ነበር። በዚህ አጋጣሚ ለሀሌታም ሆነ ሌሎች በግል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የወጣቶች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በእግርኳሳችን ላይ ነገን የተሻለ ለማድረግ እያደረጉ ለሚገኙት ጥረት ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

👉 ከጉዳት የተመለሱት እንየው ካሳሁን እና ኦሲ ማውሊ

የመጀመሪያው ዙር ፍፃሜውን ባገኘበት በዚሁ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ እና ባህር ዳር ከተማዎች ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ከጉዳት መልስ ያገኙበት ሳምንት ነበር።

ምንም እንኳን ድሬዳዋ ከተማዎች በፋሲል ከነማ የ4-0 ሽንፈትን ቢያስተናግዱም በቀኝ መስመር በኩል ማጥቃታቸውን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የቀኝ መስመር ተከላካያቸው እንየው ካሳሁን በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት መከላከያን ከረቱበት ጨዋታ በኋላ ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሶ መጫወት ችሏል። ለ72 ያህል ደቂቃዎች በሜዳ ላይ የቆየው እንየው ድሬዳዋ ከተማ እሱ ባልነበረባቸው ጨዋታዎች ያጣውን የመስመር ማጥቃት ያስታወሰ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል።

በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የባህር ዳር ከተማ ፊት አውራሪ የሆነው ኦሲ ማውሊ እንዲሁ ከወራት ጉዳት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ተመልክተነዋል። በ8ኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ፋሲል ከነማን ከገጠመ ወዲህ በባህር ዳር ከተማ መለያ ያልተመለከትነው ኦሲ ማውሊ ለሦስት ወራት ከተጠጋ ቆይታ በኋላ ወደ ሜዳ በተመለሰበት ጨዋታ ለ45 ያህል ደቂቃዎች ተሳትፎ ማድረጉ ለባህር ዳሮች አስደሳች ዜና ነው።

👉 ወንድማማቾች ግብ ያስቆጠሩበት ጨዋታ

ሀዲያ ሆሳዕናን ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ የሁለቱ “የገዛኸኝ ልጆች” ጨዋታ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ባዬ ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ሲችል በሁለተኛው አጋማሽ በዳዊት ተፈራ አማካኝነት ወደ ጨዋታው የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች የማሸነፊያዋን ግብ ሲያገኙ የግቧ ባለቤት የነበረው የባዬ ገዛኸኝ ታናሽ ወንድም የሆነው ሀብታሙ ገዛኸኝ ነበር።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ወንድማማቾች በተቃራኒ ሲገናኙ መመልከት የተለመደ ሲሆን የባዬ እና ሀብታሙን ጨምሮ በቅርቡ ሙሉዓለም መስፍን እና እንዳልካቸው መስፍንን ባገናኘው ጨዋታ እና በሌሎች በርካታ ግጥጥሞሾች እየተለመዱ የመጡ ሲሆን የዚህኛውን ለየት የሚያደርገው ሁለቱ ተጫዋቾች በተመሳሳይ በአንድ ጨዋታ ግብ ማስቆጠራቸው ነው።