የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አንደኛው ዙር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፍፃሜውን አግኝቷል ፤ ለዙሩ የመጨረሻ በነበረው የጨዋታ ሳምንት አሰልጣኞች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን እነሆ።

👉 ተለምዷዊው የዝውውር እሳቤ ይቀጥል ይሆን ?

የውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት በትናንትናው ዕለት በይፋ ተከፍቷል። ታድያ በዚህ ሂደት ከቀደሙት ጊዜያት ልምድ መነሻነት የሚጠበቁ ጉዳዮች ይኖራሉ።

በዓለምአቀፋዊው አሰራር በዝውውር መስኮት ከሦስት በላይ በቀጥታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የሚመጡ ተጫዋቾችን ማዘዋወር በቡድን ውህደት ላይ ከሚፈጥረው ተግዳሮት አንፃር የሚመከር እንዳልሆነ በማመን ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ያተኮሩ ውስን ዝውውሮች ማደረግ የውጤታማ ቡድኖች መገለጫ ነው። ይህንን ሂደት በተለይ በውድድር ዘመን አጋማሽ በሚኖሩ ዝውውሮች ላይ ደግሞ ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ ይሞከራል። በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ ፍፁም ተፃራሪ ነው።

በሊጋችን ከዚህ ቀደም ቡድኖች የፋይናንስ አቅርቦት ይኑር እንጂ የተበጀተላቸውን ገንዘብ አሟጠው ተጫዋቾችን ለማስፈሰም ሲውተረተሩ ተመልክተናል። ይህ ሂደት የአብዛኛዎቹ ክለቦች የጋራ ባህሪ ሲሆን በተለይ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ሲሆን ደግሞ በመጀመሪያው ዙር ከ10ኛ በታች ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች በሁለተኛው ዙር ዕጣ ፈንታቸውን ለመቀየር ባለ በሌለ አቅማቸው ተጫዋቾች ማዘዋወራቸው የተለመደ ነው።

ለአብነትም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በመጀመሪያው ዙር ፍፁም ደካማ ጊዜን ያሳለፉት አዳማ ከተማዎች በአጋማሹ የአሰልጣኝ ለውጥ አድርገው ከአስር የሚልቁ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው መቀላቀል ቢችሉም በመደበኛው ውድድር በሊጉ መቆየት ሳይችሉ በመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ውድድር ዳግም በሊጉ ቆይታቸውን ማረጋገጣቸው አይዘነጋም። ታድያ ከእነዚህ የጭንቅ ግዢዎች ውስጥ ሚሊዮን ሰለሞን በቻ በዘንድሮው የቡድኑ ስብስብ ውስጥ በዋና ተሰላፊነት መቀጠል ሲችል አብዛኞቹ ቡድኑን ለቀው ሂደዋል።

የዘንድሮው ውድድር በተጋመሰበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጨዋታዎች መጠናቀቂያ ላይም በነበሩ የአሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች አብዛኞቹ አሰልጣኞች በአጋማሹ ወደ ገበያ ሊወጡ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተደመጥዋል። ታድያ በገበያው ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ያተኮሩ ዝውውሮችን መፈፀም እጅግ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በዚህ እሳቤ ውስጥ ሸመታቸው የማይቃኝ ከሆነ ዝውውሮቹ በራሳቸው የታቀደላቸውን ዓላማ ከማሳካት ይልቅ ቡድኑን ለችግር የመዳረግ ዕድላቸው ሰፊ ሊሆን ይችላል።

👉 ስለአማራጭ የጨዋታ ዕቅድ ያለን የታዛባ አረዳድ

ቡድኖች ከጨዋታ ጨዋታ እንደሚገጥሟቸው ተጋጣሚዎች የተለያየ ዓይነት የጨዋታ ዕቅድን ይዘው ወደ ጨዋታ ሊገቡ ይችላሉ። ይህን በተለያዩ ምክንያቶች መተግበር ካልቻሉ ግን ፊታቸውን ወደ ሌሎች አማራጮች ሊያዞሩ ይችላሉ።

በዚህ ሂደት መሰረታዊው የሚሆነው ጉዳይ የቡድኖች የጨዋታ ዕቅድ የተጋጣሚን የጨዋታ መንገድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለውጦች ሊደረግባቸው ቢችልም በእነዚህ ለውጦች ውስጥ ግን ቡድኑ የራሱን ነገር ሳይለቅ መቀጠል ይገባዋል።

ለጨዋታዎች በሚደረጉ ዝግጅቶች ወቅት እንዲሁም በጨዋታ ዕለት ተግባራዊ የሚደረጉ የጨዋታ ዕቅዶች ሲነደፉ 70% የሚሆነው ትኩረት የራስ ቡድን ላይ ያሉ ጉዳዮች ሲሆኑ የተቀረው 30% ደግሞ የተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ እና ድክመት ላይ ከሚደረጉ ዘርዘር ያሉ ጥናቶች መነሻ የሚያደርጉ ናቸው።

በዚህ መልኩ የተዘጋጀው የጨዋታ ዕቅድ ሜዳ ላይ በሚፈለገው ደረጃ ገቢራዊ መሆን ካልቻለ ግን አሰልጣኞች ዕቅዳቸውን እንዲከልሱና ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ይህን ለማድረግ ግን የአሰልጣኞቹ በጨዋታ ወቅት ጨዋታን የመገንዘብ አቅማቸው እጅግ ወሳኝ ድርሻን ይወጣል።

በሀገራችን አውድ ግን ያለው መሰረታዊው የአረዳድ ችግር በተለየ የአማራጭ የጨዋታ ዕቅድ ጉዳይ ተደጋግሞ የሚነሳው ኳስን ለመቆጣጠር ከሚሹ ቡድኖች ጋር እንደመሆኑ ቡድኖቹ በቅብብል ተጋጣሚን ማስከፈት ሲቸገሩ ይበልጥ በቀጥተኝነት እንዲጫወቱ የመጠበቅ ይህም ካልሆነ ቡድኑ የአማራጭ የጨዋታ መንገድ ዕጥረት እንዳለበት ተደጋግሞ ሲነሳ እናስተውላለን።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የተጠየቀው የወልቂጤ ከተማ አዲሱ ዋና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ይህንን ብሏል

“እኛ ሁለተኛ ዕቅድ ብለን የምናስበው በምንፈልገው አጨዋወት ውስጥ የተሻሉ ተጫዋቾችን እያስገባን ዕድሎችም መሞከር ነው። በቅያሪዎች ጨዋታውን ለመቀየር ሞክረናል። ነገር ግን ሊሳካልን አልቻለም።” ሲል ተደምጧል።

በምላሹ ውስጥ የአሰልጣኙ ዕምነት በእግርኳሳችን ገዢ እየሆነ ከመጣው አስተሳሰብ የተለየ ስለመሆኑ ማስተዋል ይቻላል። ይህም ሁለተኛ የጨዋታ ዕቅዱ በመጀመሪያው እሳቤው ውስጥ መጠነኛ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ውስጥ ስለመሆኑ ሀሳቡን ሰጥቷል።

ሁለተኛ ዕቅዶች እንደ አሰልጣኞች ዕምነት ከመጀመሪያው አንፃር ዝምድናም ሆነ ፍፁም ልዩነት ሊኖራቸው ቢችልም በሀገራችን እግርኳስ ከገነገነው ፍፁም ተፃራሪ የሆኑ ሀሳቦችን ለመተግበር የመሞከር እሳቤ በተላቀቀ እና ዘመናዊ በሆነ አረዳድ ከመሰረታዊው የቡድን የጨዋታ እሳቤ ብዙም ሳይርቁ የመጀመሪያው የጨዋታ ዕቅድን አፈፃፀም ግምገማ ላይ ተመስርተው መጠነኛ የተጫዋች ለውጥ አልያም ሽግሽግሾችን እንዲሁም የሀሳብ ማሻሻያዎችን በማድረግ ከመሰረታዊው ነገር ሳይወጣ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሞከሩ አሰልጣኞች ብቅ ማለታቸው ተስፋ የሚሰጥ ነው።

👉 ባለአደራዎቹ አሸንፈዋል

ያሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የኮቪድ ወረርሺኝ ዳግም በሊጉ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ቡድኖች ያሉ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸው እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጨዋታቸውን ለማድረግ የተገደዱበት ሳምንት ነበር።

ታድያ በዚህ ሂደት ዋና አሰልጣኞቻቸውን ሳይዙ ጨዋታቸውን ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ በምክትሎቻቸው እየተመሩ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

በኮቪድ ውጤት መነሻነት በጨዋታ ሳምንቱ ብዙ ሲያነጋገር የቆየው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አባላት ውጤት በብዙ ውዝግቦች የታጀበ ነበር። በዚህም መነሻነት ጨዋታውን በሜዳ ተገኝቶ መምራት ያልቻለውን የቡድኑን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን አለመኖርን ተከትሎ ቡድኑን እየመራ ጨዋታውን ማድረግ የቻለው ሌላኛው የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ የሆነው ደረጀ ተስፋዬ የአዲስ አበባ ከተማውን ጨዋታ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው በተለያዩ ምክንያቶች ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ሳይዙ ወደ ሜዳ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከወትሮው በተለየ የተጫዋቾች አደረደር ባደረጉት ጨዋታ አስቀድመው ግብ አስተናግደው ለበርካታ ደቂቃዎች ሲመሩ ቢቆዩም በሁለተኛው አጋማሽ ሦስት ግቦችን አስቆጥረው መሪነታቸውን ለማስቀጠል የሚረዳቸውን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ከዚህ ቀደም የቅዱስ ጊዮርጊስ የዕድሜ እርከን ቡድኖችን በማሰልጠን ልምድ የነበረው ደረጄ ተስፋዬ በዋና ቡድን ደረጃ በዋና አሰልጣኝነት በመራው ጨዋታ ድል ማድረጉ ከጨዋታው በኋላ የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮበት የተመለከትን ሲሆን በአንፃሩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ደግሞ ከክለቡ አካባቢ ባሉ ሰዎች በተጋራ አንድ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ልጥፍ ላይ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በደስታ እና የቁጭት ስሜት ሲያነባ ተመልክተናል።

በተመሳሳይ በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በኮቪድ በመጠቃተቸው የተነሳ ጨዋታውን መምራት ባለመቻላቸው ምክትሉ ጣሰው ታደሰ ቡድኑን የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር።

በአሰልጣኝነቱ በተለያዩ ቡድኖች የዕድሜ እርከን ቡድኖች እንዲሁም ከጥቂት ዓመታት በፊት በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ይታወቃል። ይህ አሰልጣኝ በዋናነት በመራው የወልቂጤው ጨዋታ ቡድኑ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ በሁለተኝነት ለማጠናቀቅ በቅተዋል። አሰልጣኝ ጣሰው ታደሰ በሜዳው ጠርዝ ሆኖ ቡድኑን ስሜት በተሞላበት መንገድ የመራበት መንገድ እንዲሁም ግቧ ስትቆጠር እና ጨዋታው ሲጠናቀቅ ያሳየው የደስታ አገላለጽ የተለየ ነበር።

👉 አሸናፊ በቀለ ማስረገማቸውን ቀጥለዋል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በጨዋታዎች ወቅት በሚለብሷቸው አልባት ትኩረት ይስቡ የነበሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ዘንድሮም በዚህ መንገድ ቀጥለዋል።

ወደ ኋላ አዙረው ኮፍያቸውን በመልበስ የሚታወቁት አሰልጣኙ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የአድዋ ድል በዓል አስታከው ጭንቅላታቸው ላይ እንደ ነገስታት ነጭ የአንገት ልብስ ጠቅልለው በመምጣት መነጋገርያ ሆነው አሳልፈዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በፊደላት የተሞላ ከረቫት በማድረግ እንዲሁም በአንድ ጨዋታ ደግሞ በሀገር ባህል ልብስ ድምቅ ብለው ሜዳ የተገኙት አሰልጣኝ አሸናፊ ሀገራችንን ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የራሳቸውን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።