የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችን በዚህ መልኩ ተመልክተናቸዋል።

👉 የኮቪድ ወረርሺኝ ዳግም ተቀስቅሷል

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2019 አንስቶ መልኩን እየቀያየረ የዓለምን የጤና ሥርዓት እየተፈነ የሚገኘው የኮቪድ ወረርሺኝ በተወሰነ መልኩ ስርጭቱ የቀነሰ ቢመስልም በተለያዩ የኮቪድ ማዕበላት ሀገራትን ዳግም እያጠቃ ይገኛል።

በእግርኳሱ አውድ ውድድሮችን እስከመሰረዝ ድረስ ያደረሰ ጉዳትን ያስከተለው ቫይረሱ እንደሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ቀስ በቀስ ያለ ተመልካች ቀጥሎም የተወሰኑ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎችን ወደ ሜዳ በመመለስ ብቻ ጨዋታዎች እንዲደረጉ አስገድዷል። አሁን ላይ አውሮፓዊያኑ የተከተቡ ደጋፊዎችን ያለ ቁጥር ክልከላ ወደ ስታድየም እያስገቡ ህይወት ወደ ቀደመው መንገድ እየተመለሰች ይገኛል። በእኛ ሀገርም መጠኑ ቢያንስም መጠነኛ መሻሻሎችን እየተመለከተን እንገኛለን።
ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ካለው መሻሻል ባለፈ በዘንድሮው ውድድር ቫይረሱ በሜዳ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከሊጉ ውድድር ተላቆ የቆየ ቢመስልም በአንደኛው ዙር የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ግን ወረርሺኙ ዳግም ያገረሸ ይመስላል።

በሁለት ከተሞች ለ14 የጨዋታ ሳምንታት በዘለቀው ውድድር ምንም ዓይነት የኮቪድ ኬዞች ተመዝግበው ባያውቁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን በርካታ ኬዞች ስለመገኘታቸው ተነግሯል። በ15ኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች የቫይረሱ ተፅዕኖ ያለጎበኛቸው ቡድኖች እጅግ ጥቂት ናቸው። በዚህም መነሻነት ቡድኖች ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጨዋታዎች ላይ መጠቀም ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን አንዳንድ ቡድኖችም እንዲሁ አነስተኛ ቁጥር ያለውን የጨዋታ ዕለት ስብስብ ይዘው ጨዋታዎችን ለማድረግ ተገደው ተመልክተናል።

በተጨማሪነትም ሁለት ቡድኖች ጨዋታዎቻቸውን ያለ ዋና አሰልጣኞቻቸው ያደረጉበትም አጋጣሚ እንዲሁ በዚህ ሳምንት የተመለከትነው ሀነት ነበር። ምናልባት ይህ አጋጣሚ በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለክለቦች እፎይታን የሚሰጥ ቢሆንም በቀጣይ ግን ወረርሽኙ ጠንክር ብሎ መጥቶ ቡድኖች ላይ በትሩን እንዳያሳርፍ አክሲዮን ማህበሩም ሆነ ክለቦች ለስርጭቱ አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቀነስ መስራት ይኖርባቸዋል።

👉 የድሬዳዋ ደጋፊዎች ተግባር

ከ10ኛ የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ ሊጉን በማስተናገድ ላይ የምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ ለወትሮም ቢሆን እንግዶችን በፍቅር ተቀብሎ በማስተናገድ ወደር የማይገኝላት መሆኗን አሁንም አስመስክራለች።

በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን የምስራቅ ኢትዮጵያው ብቸኛ የሊጉ ተወካይ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው የተሻለ ውጤት ይሰበስብባቸዋል ከተባለላቸው ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች አምስቱን ብቻ አሳክቶ በከተማው የነበረውን ቆይታ አጠናቋል።

በተለይ በመጨረሻ ጨዋታቸው ደግሞ በፋሲል ከነማ አሰቃቂ የሆነ የ4-0 ሽንፈትን አስተናግደዋል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከፍ ባለ ቁጥር በስታዲየሙ ሲታደሙ የተመለከትናቸው የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ከቡድኑ ውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ቁጥራቸው ቀንሶ ብንመለከትም በመጨረሻው የፋሲል ጨዋታ ግን “የድሬዳዋ ደጋፊ” የሚታወቅበትን ተግባር ሲፈፅሙ ተመልክተናል።

ቡድናቸው 4-0 እየተመራ እንኳን ተቃውሞ ከማሰማት ይልቅ በተመስጦ ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች በሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው ግቦችን ከማስቆጠር አልፎ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉትን የፋሲል ተጫዋቾች በተለይም ኦኪኪ አፎላቢ እና በረከት ደስታ ተቀይረው ሲወጡ እጅግ አስገራሚ አድናቆት ቸረዋቸዋል።

በዚህ ያላበቃው ተግባራቸው ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በተመሳሳይ ለፋሲል የቡድን አባላት ያሳዩት ድጋፍ የሚያስገርም ነበር። ታድያ ሰላማዊ በሆነ የእግርኳስ ፉክክር በብቃት ላሸነፈ ቡድን መሰል ክብር ማሳየት ሊለመድ የሚገባ አይደለምን ?

👉 ጉዳት ያስተናገዱት የመሀል ዳኛ

በእግርኳስ ጨዋታ ጉዳት ያስተናገዱ ተጫዋቾች አለፍ ሲልም ተመልካቾችን ተመልክተን እናውቅ ይሆናል ነገርግን የጨዋታ አርቢትሮች ጉዳት ሲያስተናግዱ ብዙም የተለመደ አይደለም።

ሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና ያገናኘው የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግጥሚያ ላይ የዕለቱ የመሐል ዳኛ የነበሩት አዳነ ወርቁ በጨዋታ ሂደት 10ኛው ደቂቃ ላይ ከሲዳማ ቡናው የመሐል ተከላካይ ያኩቡ መሐመድ ጋር በመጋጨታቸው የተነሳ ጉዳትን አስተናግደዋል።

አርቢትሩ የመጀመሪያ እርዳታ ቢደረግላቸውም ጨዋታውን መቀጠል አለመቻላቸውን ተከትሎ ለ4ኛ ዳኛው ተከተል ተሾመ ኃላፊነቱን አስረክበው ለተሻለ ህክምና ወደ ሆስፒታል ያመሩበት አጋጣሚ የሳምንቱ ሌላኛው ትኩረት የሳበ ክስተት ነበር።

ትናንት ባወጣነው ዜና መሰረት የመሀል ዳኛው የደረሰባቸው ጉዳት ለክፉ እንደማይሰጥ ታውቆ ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ አሁን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ማስነበባችን ይታወሳል።

👉 የድሬዳዋ ውድድር ሲጠቃለል

ከ10ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ሊጉን የማስተናገድ ተራውን ከሀዋሳ ከተማ የተረከበችው ድሬዳዋ ከተማ በሰላሳ ስድስት ቀናት ለስድስት የጨዋታ ሳምንታት የተሰጣትን አርባ ስምንት ጨዋታዎችን የማስተናገድ ኃላፊነት በብቃት መወጣት ችላለች።

ፍፁም የተዋጣለት ውድድርን ማስተናገድ የቻለችው ድሬዳዋ ከተማ ከሌሎች ውድድሮች በተሻለ መልኩ አምና ብዙ ወቀሳ ይቀርብበት የነበረውን የመጫወቻ ሜዳን ለዚህኛው ውድድር አሻሽለው የቀቡበት መንገድ ለሌሎች አስተናጋጅ ከተማዎች ለመማርያነት በምሳሌነት መቅረብ የሚችል ስለመሆኑ ይታመናል።

በተለይም በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት በከተማው ከፍተኛ ዝናብ ቢጥልም ይህ ሂደት የጨዋታውን መልክ እንዳበላሽ በማሰብ በጨዋታዎች ወቅት ያደርጉት የነበረው ጥረት እንዲሁ ሌላው አድናቆት የሚቸረው ተግባር ነበር።

ከዚህ ባለፈም በመለማመጃ ሜዳ ሆነ በሆቴል እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች መልካም የነበረው ውድድሩ በቀጣይ ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ የማስተናገድ ተራውን ለአዳማ ከተማ አስረክባለች። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ዋና ነጥብ ሀገራችን ባላት አቅም እንከን አልባ ውድድሮችን ከአዘጋጅ ከተሞች መጠበቅ የዋህነት እንደሆነ ነው። ነገር ግን በዋነኝነት ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ከተሞች ከመጨረሻው ውድድር የማሰናዳት ልምዳቸው ጥቂትም ቢሆን ተሻሽለው ለመቅረብ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ነው። ይህ ከሆነ እና በየጊዜው እንደሚኖራቸው አቅም መጠነኛ ለውጦችን እያደረጉ ከቀጠሉ በጊዜ ሂደት ውድድሩ እና እግርኳሳዊ ክንውኖችን የማስተናገድ አቅማችን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ማለቱ የሚቀር አይሆንም።

👉 አድዋ ተዘክሯል

ለመላው አፍሪካዊያን የኩራት ምንጭ የሆነው የአድዋ ድል በዓል በትናንት በስቲያ በመላው ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተዘክሯል። በእግርኳሱም በዕለቱ በድሬዳዋ ዓለምአቀፍ ስታዲየም የተደረጉት ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ይህ በዓል በደማቁ የተዘከረበትን አጋጣሚ ፈጥረው አልፈዋል።

በሁለቱም ጨዋታዎች በጦርነቱ ለተሰው ጀግኖች የአበባ ጉንጉን የተቀመጠ ሲሆን በተጨማሪነትም ጀግኖቹ በጭብጭባ ተወስተዋል። ከዚህ ባለፈ በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ በስታዲየሙ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች የተበተኑ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በማርሽ ባንድ በመታጀብ ተዘምሮ ጨዋታው ጅማሮውን አድርጓል።

አምናም በባህር ዳር በነበረው ውድድር በተመሳሳይ ይህን ታላቅ ቀን የተዘከረ ሲሆን መሰል ልምምዶች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው ይታመናል።