የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 13ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 13ኛ ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ተካሂዶ በመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲ ነጥብ ሲጥል ንግድ ባንክ አሸንፏል።

ረፋድ 4፡00 ሀላባ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። እንደ ቡድን በመጫወት በተደራጀ የማጥቃት ሽግግር ውስጥ በመግባት የሀላባን እንቅስቃሴ ገና በጨዋታው ጅማሬ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ነጌሌዎች ግልፅ ሦስት የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ምስጋናው ግርማ በግንባሩ በመግጭት በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣው እና ብዙም ሳይቆይ ግራ መስመር አቅጣጫ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት አቤል ፈንታ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ለአርሲዎች የሚታስቆጭ ጎል አጋጣሚዎች ነበሩ።

ሁለቱም በኩል ጨዋታው ቀዝቀዝ እያለ ቢሄድም ከውሃ እረፍት በኃላ ነጌሌዎች ከመስመር እየተነሳ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ትልቁን ሚና ሲወጣ የተመለከትነው ብሩክ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ለጎሉ ቅርበት ላይ የሚገኘው ፍቅሩ ጴጥሮስ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ወደ ሰማይ የሰደዳት ሌላኛው ጥሩ ሙከራ ሆኖ ያለፈ ነው። አልፎ አልፎ በረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት በመሄድ ወደ ጨዋታው ለመግባት ጥረት ያደረጉት ሀላባዎች የተሳካ የጎል ዕድል መፍጠር ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በመልሶ ማጥቃት ድንገተኛ ጥቃት የሰነዘሩት ሀላባዎች በ58ኛው ደቂቃ በሙሉጌታ ተሾመ አማካኝነት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥረዋል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ የአቻነት ጎል ፍለጋ በሙሉ ኃይላቸው ያጠቁት ነጌሌዎች በ68ኛው ደቂቃ በጥሩ መንገድ የተላከለትን ብቻውን ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በጥሩ አጨራረስ ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ቶማስ ነገሌዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ወደፊት የሚሄዱት ነገሌዎች በሚፈጥሩት ክፍት ሜዳ ለመጠቀም ያሰቡት ሀላባዎች ተቀይሮ በገባው ማናዬ ፋንቱ አማካኝነ ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ጨዋታውም በጥሩ የዳኝነት እንቅስቃሴ ታጅቦ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጌሌዎች በጊዜያዊነትም ቢሆን ምድቡን የሚመሩበትን ዕድል ሲያገኙ ሀላባ ከተማዎች ባሉበት ደረጃ ረግተዋል።

ደብዘዘ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተደረገበት የ8፤00 የባቱ ከተማ እና የጋሞ ጨንቻ ጨዋታ በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል። ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት የተሻለ በመሆን ባቱዎች ጥሩ ቢሆንም ግልፅ የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር በሠላሳ ደቂቃ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል። ከግራ መስመር ከተከላካይ ጀርባ ፍሬው ዓለማየሁ የተጣለለትን በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት የጋሞ ጨንቻው ግብጠባቂው ቢያድንበትም ብዙም ሳይቆይ በ36ኛው ደቂቃ የጋሞ ጨንቻዎች ተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ያሬድ ወንድማገኝ ባቱን ቀዳሚ የምታደርግ ጎል አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በጥሩ የፉክክር ግለት ሲቀጥል ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተደጋጋሚ ጫና መፍጠር የቻሉት ጋሞች በተለይ አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ በአንዴ ያደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ቅያሬ ተሳክቶላቸው በ61ኛው ደቂቃ ግቡ ፊት ለፊት ከአስራ ስድስት ሀምሳ ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው አስቻለው አታ በግሩም ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

በዚህች ጎል የተነቃቁት ጋሞዎች ከአራት ደቂቃ በኃላ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በተመለከትነው ለገሠ ዳዊት አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረው ነበር። ከዕረፍት መልስ እንደወሰዱት ብልጫ ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኛሉ ተብሎ ሲጠበቅ በመጨረሻው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሄኒካ ሄይ ባቱዎችን አቻ ያደረገች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የደረጃ መሻሻል ሳያሳዩ በዛው ለመቆም ተገደዋል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የጌዲዩ ዲላ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ከብልጫ ጋር ንግድ ባንኮች 3-1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወጣቱ የመስመር አጥቂ አደም አባስ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ከመስመር ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት አክርሮ የመታውን ኳስ በ5ኛው ደቂቃ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ጎል የደረሱት ባንኮች በ24ኛው ደቂቃ የኃላሸት ሰለሞን በቀድሞ አሳዳጊ ክለቡ ላይ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር መሪነታቸውን ማስፋት ችሏል። ለዚህች ጎል መቆጠር የአባይነህ ፌኖ አስተዋፆኦ የጎላ ነበር።

የንግድ ባንኮችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የተሳናቸው ጌዲዩዎች የረባ የጎል እድል ሳይፈጥሩ ሦስተኛ ጎል ለማስቆጠር ተገደዋል። 30ኛው ደቂቃ ወሰኑ አሊ በቀኝ መስመር ተጫዋች ቀንሶ በማለፍ አመቻችቶ ያቀበለውን የኃላሸት ሰለሞን ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ሦስት ጎል ማስቆጠራቸው በተወሰነ መልኩ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠባቀቅ በተቃረበበት ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከትኩረት የወጡት ንግድ ባንኮች ከሳጥን ውጭ በሰሩት ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት ሙሉቀን ተስፋዬ ግሩም ጎል ለጌዲዩ ዲላ ማስቆጠር ችሏል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ከዕረፍት መልስ የነበረው እንቅስቃሴ ፈጣን ያልነበረ መሆኑን ተከትሎ ብዙም የጎል ዕድሎች ሳይፈጠሩበት ጨዋታው በንግድ ባንክ 3-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንኮች ወደ መሪዎቹ ሲጠጉጌዲዩ ዲላ ስምንተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል።