የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት የዛሬ ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የ3ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ጎንደር ላይ ሦስት የምድብ ሀ ጨዋታዎች ተደርገው ንግድ ባንክ፣ ሰበታ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አሸንፈዋል።

ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም 4፦00 ላይ ሲዳማ ቡናን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ በሲዳማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በረፋዱ ጨዋታ ላይ ሲዳማ ቡናዎች በ24ኛው ደቂቃ ፍቅር ግዛቸው ባስቆጠራት ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል። ሲዳማ ቡናዎች የያዙትን መሪነት ለማስጠበቅ በተደጋጋሚ ስዓት የመግደል ስልት መጠቀማቸው ጨዋታውን አሰልቺ መልክ እንዲኖረው ያደረገ ሲሆን ስታዲየሙ ላይ የተገኘውን የስፖርት ቤተሰብንም ያስከፋ ክስተት ነበር።

በመቀጠል 8:00 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከወላይታ ድቻ ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው ላይ ግብ በማግባቱ ቀዳሚ የነበሩት እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ግብ በፍጥነት ይደርሱ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሲሆኑ በ25ኛው ደቂቃ ኢዮብ ተስፋዬ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር ድቻን ቀዳሚ መሆን ችለው ነበር። መሐል ሜዳ ላይ ጥሩ የነበሩት ባንኮች በአንፃሩ በዚህ አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ባንኮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ያገኙት በቶሎ ነበር። በ51ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተተፋን ኳስ ዳዊት ዮሐንስ ወደ ግብ ቀይሮት አቻ መሆን የቻሉ ሲሆን ዳዊት ዮሐንስ በድጋሜ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ግሩም ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ ባንክን መሪ ማድረግ ችሏል ። ዳዊት ዮሃንስ በመጀመሪያው ሳምንት ባንክ ከባህርዳር ጨዋታ በቀይካርድ ከሜዳ ተሰናብተቶ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ከቅጣት መልስ ለባንክ ሁለቱን ያሸናፊነት ግቦች አስቆጥሯል። ወላይታ ድቻዎች በጨዋታው መገባደጃ ላይ አቻ የሚሆኑበትን ወርቃማ እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም 89ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

የዕለቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር 10:00 ላይ የተደረገው የሰበታ ከተማ እና ሀላባ ከተማ ጨዋታ ሲሆን በ2 -1 በሰበታ አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ በነበረው ጨዋታ ሰበታ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅሰቃሴ በማድረግ 39ኛው ደቂቃ በፋሲካ መስፍን አማካኝነት ቀዳሚ በመሆን 1-0 እየመሩ ወደ እረፍት ያመሩ ሲሆን በአጋማሹ በሀላባ በኩል የረባ ሙከራ አልተደረገም።

ከእረፍት መልስ በ55ኛው ደቂቃ ላይ አብዱ ጀማል ሳጥን ውስጥ ወደግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂ ተጨርፎ ብረት የመለሰበት በሙከራ ደረጃ የሚጠቀስ ነበር። በሰበታ በኩል በ61ኛው ደቂቃ ዳዊት አበራ በስቆጠረው ግብ 2 – 0 መምራት የጀመሩ ሲሆን 77ኛው ደቂቃ ላይ ሀላባዎች በታምራት አበራ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጫና ማድረግ ቢጀምሩም እንደ ረፋዱ ጨዋታ ሁሉ ሰበታዎች በተደጋጋሚ በመውደቅ ሰዓት ለመግል ሲጥሩ ታይቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሰበታ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።