[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የድሬዳዋ ከተማ ክለብ ቦርድ ሙሉ በሙሉ ነባር የአሠልጣኝ ቡድኑን በማሰናበት በአዳዲስ አሰልጣኞች ለመተካት ሥራ ጀምሯል፡፡
በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ስኬት እየራቀው የመጣው ድሬዳዋ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር አመት አጋማሽ ቡድኑን በመረከብ ክለቡን የማቆየት ሀላፊነትን የተወጡትን አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ኮንትራት ለሁለት ተጨማሪ አመት በማራዘም ወደ ውድድር ቢገባም አሠልጣኙ ክለቡ ከጠበቀው በታች ውጤት በማስመዝገቡ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በመጥቀስ የመጀመሪያው ዙር ስድስት ጨዋታዎች እየቀሩ አሰልጣኙን ከመንበራቸው በማገድ በክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር ፉአድ የሱፍ እና ረዳቶቻቸው እየተመራ ውድድሩን አጋምሷል። አሰልጣኞቹ በከተማዋ የነበረውን ውድድር በአግባቡ ባለ መወጣታቸው እና ከተጠበቀው በታች ውጤት በማስመዝገብ ክለቡ በ16 ነጥቦች በ9 የግብ ዕዳ አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ክለቡ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል።
ይህንን ውጤት በመንተራስ የክለቡ ቦርድ ከሰሞኑ ጥልቅ ውይይትን ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በውይይቱም የክለቡ አሰልጣኞች ለውጤቱ መጥፋት ተጠያቂ ናቸው በማለት ክለቡን በጊዜያዊነት ሲመሩ የነበሩት ፉአድ የሱፍን እና ረዳት የሆኑት ቶፊክ እንድሪስ፣ ኤፍሬም ጌታሁን እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ አምባዬ በፍቃዱን ከዋናው ቡድን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ያነሳ ሲሆን ቡድኑን በቡድን መሪነት ሲመራ የነበረውን የቀድሞው ተጫዋች ቶፊቅ ሀሰንንም በተመሳሳይ ከቦታው መነሳቱ ይፋ ሆኗል፡፡ ይህንን ቆራጥ እርምጃ የወሰደው ድሬዳዋ ከተማ ለሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር ዋና አሰልጣኝን ጨምሮ አዳዲስ ረዳቶችን ለመሾም የምርጫ ሂደት ላይ መሆኑንም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡