የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 13ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ትናንት የጀመረው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የ13ኛ ሳምንት ዛሬ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ኤሌክትሪክ ነጥብ ሲጥል ሻሸመኔ ከመመራት ተነስቶ አሸንፏል።

ስምንት ሰዓት በጀመረውና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አምቦ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያለምንም ጎል ተጠናቋል። ሳቢ ፉክክር በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ የምድቡ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ኳሱን ተቆጣጥረው የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን በፀጋ ደርቤ እና በምንያህል ተሾመ አማካኝነት ቢያደርጉም የአምቦን ጠንካራ የመከላከል አጥርን አልፈው ጎሎችን ማስቆጠር ተቸግረው ቆይተዋል።

በአንፃሩ አምቦዎች ብልጫ ቢወሰድባቸው በተለይ በረጃጅም ኳሶች ወደፊት በመሄድ የኤሌክትሪኮችን መረብ መፈተሽ ችለዋል። የአምቦዎቹ የፊት አጥቂ የጫላ በቀለ እንቅስቃሴም ኢትዮ ኤሌክትሪክን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲረብሻቸው ውሏል። በ22ኛው ደቂቃ ከአምቦ የመከላከል ቀጠና በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ አሚር አብዲ አፈትልኮ በመግባት ከግብጠባቂው ዘሪሁን ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ዘሪሁን እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣበት እና ይሄው ኳስ የመዐዘን ምት ተሻምቶ የአምቦው ተከላካይ በዳሳ ታሪኩ በግንባር ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በአስደናቂ ሁኔታ የመለሰበት ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሙከራዎች ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት እና በህብረት በከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ወደ ሜዳ የገቡት አምቦዎች ነብዩ ንጉሡ እና ነቢል አብዱሰመድ የፈጠሩትን ግልፅ የጎል ዕድል ከፍተኛ ልምድ ያለው ኤሌክትሪኮች ግብጠባቂ ዘሪሁን ታደለ ባያመክንባቸው ኖሮ ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችሉበት አጋጣሚ በተፈጠረ ነበር።

ምድቡን የመምራት ፍላጎታቸውን ለማሳካት በተቆራረጠ ኳስ ወደፊት በመሄድ አልፎ አልፎ ሙከራ ያደረጉት ኤሌክትሪኮች በ69ኛው ደቂቃ መሪ ለመሆን ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ናትናኤል ጋንጁላ ከሳጥን ውጭ የመታውን ጠንካራ ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። 80ኛው ደቂቃ ደግሞ ፀጋ ደርቤ ሳጥን ውስጥ ከግብጠባቂው ጋር ቢገናኝም ተንሸራቶ አድኖበት ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተከታዩ በአንድ ነጥብ በልጦ መሪ ሲሆን አምቦ ከተማ ከደረጃው ግርጌ ባለበት ተቀምጧል።

አስር ሰዓት የተሰደረገው የሻሸመኔ ከተማ እና የገላን ከተማ ጨዋታ በድራማዊ ክስተት ታጅቦ በሻሸመኔዎች 3–2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጥሩ እግርኳስን የሚጫወቱት ገላኖች በጨዋታው ጎል ለማስቆጠር ብዙም አልተቸገሩም ነበር። ከአማካዩ በየነ ባንጃ የግል ጥረት የጀመረው ኳስ ሳጥን ውስጥ ደርሶ በ10ኛው ደቂቃ በኃይሉ ወገኔ አማካኝነት የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። ከመስመር እየተነሳ አደጋ ክልል ውስጥ በመግባት ጎል ለማስቆጠር ይጥር የነበረው የቀድሞ ከአዳማ ታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ሲጫወት የምናቀው የኃላሸት ፍቃዱ ብዙም ሳይቆይ በ12ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ጫና ፈጥረው በተደጋጋሚ ወደ ፊት እየሄዱ የጎል ዕድል መፍጠራቸውን የቀጠሉት ገላኖች በየነ ባንጃ ከ እንዲሁም የኃላሸት ጎል መጠናቸውን ማስፋት የሚችሉበትን ዕድሎችን ሳይጠቀሙ መቅረታቸው በስተመጨረሻ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል።

ወደ ዕረፍት መዳረሻ 45ኛው ደቂቃ የገላን ተከላካዩችን መዘናጋት ተከትሎ ቦና አሊ ሻበመኔዎችን ተነቃቅተው ከዕረፍት እንዲመለሱ የምታደርግ ጎል አስቆጥሯል። በሁለተኛው አጋማሽ የመሐል ሜዳ ክፍል ላይ የገላን ተጫዋቾች በቅብብሎሽ የፈጠሩትን ስህተት ተከትሎ ቦና አሊ ሻሸመኔዎችን ወደ ጨዋታ የመለሰች ጎል ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በ51ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

በቀሩት ደቂቃዎች ሻሸመኔዎች ከመመራት ሁለት ጎል በማስቆጠር ሲነቃቁ በአንፃሩ ገላኖች በእንቅስቃሴ ወርደው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ቢሄድም አልፎ አልፎ በሁለቱም በኩል ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ይደረጉ ነበር። ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል ተቀይሮ የገባው የሻሸመኔው የመስመር አጥቂ ኑሪ አማን የገላኑ ግብጠባቂ ስህተት ታክሎበት ቡድኑን ከመመራት ተነስቶ አሸናፊ እንዲሆን ያስቻለች ወሳኝ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሻሸመኔ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።