የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ 13ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ የ13ኛው ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው መሪው ነቀምቴ ከተማ ከሀምበሪቾ ነጥብ ሲጋራ ተከታዩ ኢትዮጵያ መድን አሸንፏል፡፡

8፡00 ላይ ፌዴራል ፖሊስን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን 1-0 አሸንፏል። በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን አጥቂው ያሬድ ዳርዛን መሠረት ባደረገ እንቅስቃሴ መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል፡ ፌዴራል ፖሊሶች በአንፃሩ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ ስልትን በመጠቀም አልፎ አልፎ በሚያገኙት ዕድል ለመጠቀም ቢሞክሩም መድኖች በመስመር እና በመሀል ሜዳ ጥምረት ቅንጅት ወደ አጥቂው ያሬድ አድልተው በመጫወት ብልጫን ሲወስዱ ተመልክተናል፡፡

ነገር ግን የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ መድኖች ከነበራቸው ብልጫ አንፃር ልዩነት ይፈጥራሉ ተብሎ ቢጠበቅም በቀላሉ ወደ ሳጥን ጠርዝ ሲደርሱ የሚያሳዩት ደካማ የአፈፃፀም ተግባር ይህ ነው የሚባልን አጋጣሚዎች እንዳንመለከት አግዶናል፡፡ በእንቅስቃሴ የተገደቡ ይመስሉ የነበሩት ፌድራል ፖሊሶች በአንፃሩ ከተሻጋሪ ኳሶች ሁለት ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡ 25ኛው ደቂቃ ላይ እሱባለው ፍቅሬ ከቀኝ በኩል ያሻገረውን ኳስ ታምራት ኢያሱ በግንባር ገጭቶ ጆርጅ ደስታ የያዘበት እና 38ኛው ደቂቃ እቡባለው ከግራ በኩል ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ በድጋሚ ጆርጅ የያዘበት ሊጠቀሱ የሚችሉ የአጋማሹ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ሊያመሩ አንድ የጭማሪ ደቂቃ ሲቀር ከገላን ከተማ መድንን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው ኪቲካ ጅማ በመልሶ ማጥቃት የደረሰውን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና በቀጥታ ወደ ጎል ቢመታትም በተከላካዮች ተጨርፋ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡

ከእረፍት መልስ አሰልቺ ይዘትን በተላበሰው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም ለዕይታ ማራኪ ነበረ ለማለት የሚይቻል አልነበረም፡፡ ነገር ግን በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ወደ ሜዳ የገቡት መድኖች በተደጋጋሚ ዕድልን ለመፍጠር ቢጥሩም ኳስን ከመረብ በማገናኘቱ አልታደሉም፡፡ የመድኖችን የቅብብል ስህተት እየጠበቁ ቀዳዳ ፍለጋ ላይ ተሰማርተው በዚህኛው አጋማሽ ፌዴራል ፖሊሶች ተሽለው ቢታዩም ራስ ወዳድ የሆኑ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸው የኃላ ኃላ ቡድኑን ዋጋ አስከፍለዋል፡፡ በያሬድ ዳርዛ የርቀት ሙከራ ወደ ፌድራል ፖሊስ የግብ ክልል መድኖችን ከ60ኛው ደቂቃ ገደማ በኋላ በማድረግ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል፡፡ ቻላቸው መንበሩ ከመስመር አሻምቶ አብዱለጢፍ ሙራድ ነፃ ሆኖ አግኝቶ የሳታት እና እዮብ ገብረማርያም የግል ብቃቱን ተጠቅሞ መቶ በዮሐንስ ደረሱ የተመለሰበት ሌላኛዋ ሙከራ ነበረች፡፡

የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃ ሙሉ በሙሉ ጫና ፈጥረው ግብን ለማግኘት ትግል ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ መድኖች 86ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አግኝተዋል፡፡ በቀኝ የፖሊሶች የግብ ክልል ጠርዝ አካባቢ አማካዩ አማካዩ በኃይሉ ኃይለማርያም በቀጥታ አክርሮ ሲመታ የግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደረሱ የቦታ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ኢትዮጵያ መድን መሪ ሆኗል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ መቆጠር ሳይችል ጨዋታው 1ለ0 በመድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ድሉም መድን ከመሪው ነቀምቴ በአንድ ነጥብ አንሶ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

በ10፡00 የተደረገው የሀምበሪቾ እና ነቀምቴ ከተማ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ጥሩ ፉክክርን ከጅምሩ ማሳየት የጀመረው ጨዋታው ጎልን ገና በጊዜ ነበር ያስመለከተን። አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ከተረከቡት በኋላ መሻሻሎችን በሁለተኛው ዙር እያሳየን የሚገኘው ሀምበሪቾ ዱራሜ 2ኛ ደቂቃ ላይ የቀድሞው የደደቢት የመስመር ተጫዋቾች ዳግማዊ ዓባይ ከማዕዘን ሲያሻማ በወላይታ ድቻ የምናውቀው ዮሴፍ ድንገቶ ከተከላካዮች መሀል አፍትልኮ በመውጣት በግንባሩ ግሩም ጎል አስቆጥሮ የተራራ አናበስቶቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ከየትኛውም ቦታዎች ኳስን ሲያገኙ በረጃጅሙ በማሻገር በግንባር ለማስቆጠር አጥቂው ኢብሳ በፍቃዱን ማዕከል አድርገው ነቀምቴዎች ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ በተረጋጋ የኳስ ቅብብል ሀምበሪቾዎች ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት አድርገው በተለይ ልዑልሰገድ አስፋው እና ቤዛ መድህን ቶሎ ቶሎ በማሻገር ተጨማሪ ግብን ቡድናቸው እንዲያገኝ ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡

አጋማሹ ሊገባደድ አራት ደቂቃ ሲቀረው የነቀምቴ ተከላካዮችን ስህተት ለመጠቀም ቤዛ መድህን ቢጥርም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በአንፃራዊነት በረጃጅም ኳሶች አቻ ለመሆን ቀያይ ለባሾቹ ነቀምቶች ጥረት ማድረግ ቢችሉም የቀድሞው የወላይታ ድቻ እና የአሁኑ የሀምበሪቾ ዱራሜው ግብ ጠባቂ አስራት ሚሻሞ አስደናቂ ብቃት ተጨምሮበት በ1ለ0 ተመሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴን በሂደት ግን የነቀምቴ ከተማ ተሻገሪ ኳሶች አይለው የታየበት ነበር ማለት ያስችላል፡፡ ይሁንና የዕለቱ ዳኛ ተካልኝ ለማ የጨዋታው ግለት ከፍ እያለ ሲመጣ ለመቆጣጠር የሚያደርጉበት መንገድ እምብዛም አልነበረም፡፡ 62ኛው ደቂቃ ላይ ነቀምቴዎች ገመቺስ አማኑኤል ከቀኝ የሀምበሪቾ የግብ ክልል አካባቢ አክርሮ ሲመታ በዕለቱ ድንቅ የነበረው አስራት ሚሻሞ ሲመልሰው በድጋሚ አምበሉ ቴዎድሮስ መንገሻ እግር ስር ገብታ በድጋሚ ወደ ጎል ቢመታም ሂደር ሙስጠፋ ተንሸራቶ አውጥቷታል፡፡

በመልሶ ማጥቃት አማራጭ በተለይ ቤዛ መድህንን ኢላማ ባደረገ መልኩ ለመጫወት ሀምበሪቾዎች ሞክረዋል፡፡ ቤዛ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወደ ሳጥን ገብቶ ያመከነው እና ዳግማዊ ዓባይ በዚሁ የጨዋታ ሂደት ወደ ግብ ሲልክ ተመስገን ዱባ በግንባር ገጭቶ የወጣበት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ነቀምቴዎች በረጃም ኳስ ጥቃት ወደ መሰንዘሩ ገብተዋል፡፡ ከሳጥን ውጪ ዋቁማ ዲንሳ መቶ የግቡ ቋሚ የላይኛው ብረት የመለሰው እንዲሁም ደግሞ ኪዳኔ አሰፋ በሰራው ስህተት ተነጥቆ ዳንኤል ዳዊት በቀጥታ ሲመታ በሚያስቆጭ መልኩ በድጋሚ የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል፡፡

ነገር ግን 80ኛው ደቂቃ ወደ ጎል የተሻገረ ኳስ ላይ ግብ ጠባቂው አስራት በቴዎድሮስ መንገሻ ላይ ኳስን ለመያዝ ሲሞክር ጥፋት በመፈፀሙ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳንኤል ዳዊት ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን አቻ አድርጓል፡፡ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ዘርአይ ገብረስላሴ ሀምበሪቾን ወደ መሪነት ለማሸጋገር ያቃረበች አጋጣሚን አግኝቶ የነበረ ቢሆን መጠቀም ሳይቾል ቀርቶ ጨዋታው 1ለ1 ተደምድሟል፡፡

በሁለቱ የዛሬ የምድቦቹ ጨዋታዎች ላይ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ፣ የአርባምንጭ ከተማው መሳይ ተፈሪ ፣ የሀድያ ሆሳዕናው ሙሉጌታ ምህረት ፣ የወልቂጤ ከተማው ተመስገን ዳና እና የአዳማ ከተማው ረዳት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ተጫዋቾችን ተመልክቶ ለማስፈረም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ታድመው ተመልክተናል፡፡