​የካፍ ላይሰንስ የስልጠና ማንዋል የማዘጋጀቱ ሂደት በድጋሚ ተጀምሯል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ኢትዮጵያዊያን የካፍ ኢንስትራክተሮች በክረምቱ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሊሰጥ ለታቀደውን የአሰልጣኞች የላይሰንስ ስልጠና ሰነድ የማዘጋጀቱን ሥራ በቢሾፍቱ ከተማ ጀምረዋል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር (ካፍ) ያለፉትን ሦስት አመታት አፍሪካ ውስጥ የሚሰጡ የሲ ፣ ቢ እና ኤ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠናን ከጥራት እና ከማሰልጠኛ በቂ ክህሎት ማነስ ጋር በተገናኘ ሙሉ በሙሉ አቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ካፍ በድጋሚ በርካታ የማሻሻያ እንዲሁም አዳዲስ የስልጠና መመሪያዎችን ከነደፈ በኋላ ከተጠናቀቀው የፈረንጆቹ አመት ጀምሮ በተለያዩ የአህጉሪቱ ሀገራት የዲ ላይሰንስን በአዲስ መልኩ በማካተት እንዲጀመር አድርጓል። በሀገራችን ኢትዮጵያም የዲ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና በአንድ ዙር ሰላሳ ሰልጣኞችን በማካተት ለአስር ቀናት በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች መሰጠት ከጀመረ የሰነባበተ ሲሆን የሲ፣ ቢ እንዲሁም ደግሞ የኤ ላይሰንስ ስልጠና ከዲ ላይሰንስ የተለየ ይዘት ያለው በመሆኑ እና ካፍም ያስቀመጠው መመሪያ ጠንከር በመሆኑ እስካሁን አልተጀመረም። በያዝነው የ2014 መጨረሻ ክረምት ወር ላይ ግን ሀገራችን ከረጅም አመታት በኋላ ይህ የላይሰንስ ስልጠና በይፋ እንደምትጀምር ይጠበቃል።

ለዚህም ስልጠና ይረዳ ዘንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የወንድ እና የሴት የካፍ ኢንስትራክተሮች በክረምቱ ሊሰጥ ለታቀደው ስልጠና የሚሆን ማንዋል ለማዘጋጀት ከወራት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ መቀመጫቸውን በማድረግ የማዘጋጀቱን ተግባር ሲከውኑ የነበረ ሲሆን አሁንም በድጋሜ ማኑዋሉን ካፍ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት ለማዘጋጀት ኢንስትራክተሮች ከትላንት ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ ቶም ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ የዝግጅት ስራቸውን ጀምረዋል፡፡ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው የማንዋል ቅድመ ዝግጅት ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ በክረምቱ የሲ ፣ የቢ እና የኤ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት እንደሚጀምርም ይጠበቃል።