ካፍ ለሴት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ኢንስትራክተሮች ስልጠና መስጠት ጀመረ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ካፍ ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ጋር በጋራ በመሆን ለአፍሪካ የሴት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ኢንስትራክተሮች የፊትነስ አሰጣጥ ስልጠናን መስጠት ጀምሯል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር ( ካፍ) በአህጉሪቱ የሴቶች እግር ኳስ አሁን ካለበት ደረጃ ፈቀቅ ብሎ መገኘት እንዲችል የተለያዩ ስራዎችን ባቋቋመው የሴቶች ልማት እና ዕድገት ኮሚቴ ስር በርካታ ስራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡ ከእነኚህም መካከል በየጊዜው ስልጠናዎች በመዘርጋት የሴት እግር ኳስንም ሆነ የሴት ባለሙያዎችን ለማብቃት አበረታች የሆኑ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳደሪ አካል ከሆነው (ፊፋ) ጋር በጣምራ በመሆን በአፍሪካ ሴት ብሔራዊ ቡድንን በመያዝ እያሰለጠኑ ላሉ ባለሙያዎች እና ሴት ለሆኑ ኢንስትራክተሮች ትኩረቱን በስፋት ፊትነስ ላይ ያተኮረ ለዘጠኝ ቀናት የሚቆይ የኦንላይ የዙም ስልጠና በዛሬው ዕለት መስጠት ጀምሯል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል ኢንስትራክተር ሰላም ዘርዓይ በዚህ ውይይት ላይ ተካፋይ ስትሆን የሴት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ግን በዚህ ስልጠና ላይ እየተሳተፉ አይገኝም፡፡ ስለ አፍሪካ እግር ኳስ ዕድገት ፣ ስለ ቡድን ግንባታ እና የቡድን ጥንካሬ ፣ ኢንዱራንስ ፣ ስፒድ ፣ ኤጂሊቲ ፣ ዘመናዊ የዕቅድ አወጣጥ እና ፕላን ፣ የልምምድ አሰጣጥ እንዲሁም በጉዳት ወቅት ለተጫዋቾች የሚሰጡ የተሻሻሉ የማገገሚያ (Recovery) የስልጠና ሂደት እና በርካታ የፊትነስ መንገዶችን ያቀፈውን ስልጠና ወደ ስምንት የሚጠጉ ከፍተኛ የፊፋ ባለሙያተኞች እየሰጡ ይገኛል፡፡

ከእነኚህም መካከል የአሜሪካው ኢንተር ሚያሚ ክለብ የፐርፎርማንስ ዳይሬክተር ዳውን ስኮት ፣ የእንግሊዙ ኒውካስትል አካዳሚ የፊትነስ ባለሙያ ሄዲ ቶሮንቶን እና በሲዊድን እግር ኳስ ታዋቂነትን ያተረፈችሁ ሄሊና አንደርሰን ይህንን ስልጠና ከሚሰጡ ባለሙያዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ኢትዮጵያዊቷ የካፍ የሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ ባለሙያ መስከረም ታደሰ ይህንን የስልጠና ሂደት ተከታትሎ የማስፈፀሙን ተግባር እየከወነች እንደሚገኝ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡