የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን አጠናክሮ ቀጥሏል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ባለንበት የ2022 ዓመት ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ አንድ የደርሶ መልስ ፍልሚያ ብቻ የሚቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድን ለእሁዱ ወሳኝ ጨዋታ መዘጋጀቱን ቀጥሏል።

በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የ2022 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአህጉሩን የማጣሪያ ጨዋታዎች ሲያከናውን ቆይቷል። ወደ ዋናው ውድድር ለማለፍም ከጋና አቻው ጋር የመጨረሻ የደርሶ መልስ ፍልሚያውን የሚያደርግ ይሆናል። ለዚህ ወሳኝ ጨዋታ ማረፊያውን ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በማድረግ እየተዘጋጀ የሚገኘው ቡድኑ ዛሬ ረፋድም የመጀመሪያ ጨዋታውን በሚያደርግበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን አከናውኗል።

ከረፋዱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለ120 ደቂቃዎች በዘለቀው ልምምድ ላይ አሠልጣኝ ፍሬው ከረዳታቸው ምትኬ እና ከግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ፀጋዘአብ ጋር በመሆን ተጫዋቾቹ እንዲያሟሙቁ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ የግብ ዘቦች ለብቻቸው ተለይተው በግብ ብረቶቹ መሐል በአሠልጣኛቸው ስልጠና ሲወስዱ ነበር። የሜዳ ላይ ተጫዋቾቹ ደግሞ መሐል ባልገባ ይዘት ያለው እንቅስቃሴ አከናውነዋል።

በአሁኑ ሰዓት 24 ተጫዋቾችን (4ቱ ግብ ጠባቂ) የያዙት አሠልጣኝ ፍሬው በመቀጠል ቡድኑን ለሁለት ከፍለው የሙሉ ሜዳ ጨዋታ አጫውተዋል። በዚህ ሰዓት አሠልጣኙ በቶሎ ወደ ተቃራኒ ሜዳ እንዲደረስ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉም ታዝበናል። ዘለግ ያለ ደቂቃ ከወሰደው ጨዋታ በኋላም የዕለቱ የልምምድ መርሐ-ግብር ፍፃሜውን አግኝቷል። ልምምዱ ከተጠናቀቀ በኋላ አዲስ የተቀጠሩት የቡድኑ የስነ-ምግብ ባለሙያ አቶ ኢሳይያስ ለተጫዋቾቹ ላብ መተኪያ ፍራፍሬዎችን እና ሀይል ሰጪ ውህዶችን ሲሰጡ ታዝበናል።

በመጨረሻም ግዙፉ ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ከቀናት በፊት ለቡድኑ እሰጣለው ያለውን ትጥቅ ለአባላቱ አስረክቧል። በስፍራው የተገኙት የተቋሙ መስራች እና ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ከፕሮዳክሽን ማናጀሩ አቶ አቤል እና ከማርኬቲንግ እንዲሁም የኮምኒኬሽን ሀላፊው አቶ ፍፁም ጋር በመሆን ከጨዋታ በፊት የሚለበስ የማሟሟቂያ የትጥቅ ድጋፍ አበርክተዋል። ድጋፉን ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ለሴቶች ትኩረት ሰጥተው ድጋፉን በቃላቸው መሠረት በማበርከታቸው የተሰማቸውን ደስታ ሲናገሩ ተደምጠዋል። አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው ይህ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መሆኑን አውስተው ብሔራዊ ቡድኑን መደገፍ ግዴታቸው እንደሆነ በመግለፅ ቡድኑን አበረታተዋል።