​ሁለገቡ ተጫዋች ማረፊያው መከላከያ ሆኗል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከሦስት ቀናት በፊት ከአዳማ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያየው ተጫዋች መከላከያን በይፋ ተቀላቅሏል።

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው መከላከያ መጋቢት 21 ለሚጀመረው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን በሳምንቱ መጀመሪያ ቢሾፍቱ ላይ የጀመረ ሲሆን አዳዲስ ተጫዋቾችንም ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ ይገኛል። ከቀናት በፊት አሚኑ ነስሩን ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ እስራኤል እሸቱን እንዳስፈረመ መዘገባችን የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ ሦስተኛ ተጫዋች የግሉ ማድረጉን ድረ-ገፃችን አውቃለች።

ከደቂቃዎች በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ የተፈራረመው ተጫዋች ምንተስኖት አዳነ ነው። ሁለገቡ ተጫዋች ምንተስኖት 2001 ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ክለቡን በአማካይ እና ተከላካይነት ቦታ ማገልገሉ አይዘነጋም። በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ደግሞ ከአሳዳጊ ክለቡ ጋር ተለያይቶ ጉዞውን ወደ አዳማ ከተማ ቢያደርግም ከአዲሱ ክለቡ ጋር ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅሞች ጋር በተገናኘ መስማማት ተስኖት ከሦስት ቀናት በፊት በስምምነት ተለያይቷል። ተጫዋቹ በትናንትናው ዕለት ከቀድሞ ክለቡ ጋር ያለውን የወረቀት ሥራዎች ካገባደደ በኋላ ለቀጣዮቹ 16 ወራት በይፋ የመከላከያ ተጫዋች መሆኑን በፊርማው አረጋግጧል።