​”ለእሁዱ ጨዋታ በሚገባ ተዘጋጅተናል” ፍሬው ኃይለገብርኤል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከወሳኙ የጋና ጨዋታ በፊት የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም የሩዋንዳ፣ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ አቻውን የረታው ቡድኑ ወደ ዋናው ውድድር ለማለፍ ከጋና ጋር ብቻ መፋለም ይቀረዋል። የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታው የፊታችን እሁድ ከመደረጉ በፊት ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ከፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሀላፊ ጋር በመሆን ለብዙሃን መገናኛዎች ተከታዩን መግለጫ ሰጥተዋል።

“በማጣሪያው ብዙ ነገሮችን እየሰራን ነው የመጣነው። ከታንዛኒያው ጨዋታ በኋላ ብዙ እረፍት ነበር። ፌዴሬሽኑ ግን ለሴቶቹ ትኩረት ሰጥቶ ዋናውን ውድድር አቋርጦ እንድንዘጋጅ አድርጎናል። በቅድሚያ 27 ተጫዋቾችን ጠርተናል። በጥሪውም ከሁለቱም ሊጎች ለሀገር ይጠቅማሉ ያልናቸውን ተጫዋቾች አካተናል። አሁን 24 ተጫዋቾችን ይዘን እየሰራን ነው።

“የመጀመሪያ ሳምንት በቀን ሁለቴ ስንሰራ ነበር።  ከዛ በ35 ሜዳ እና ጊዮርጊስ ሜዳ እያፈራረቅን ልምምዳችንን ቀጥለናል። በታንዛኒያው ጨዋታ የተወሰነ የተጎዱ ተጫዋቾች አሉ። ይህ ቢሆንም ደስ በሚል ሁኔታ ልምምዳችንን እየሰራን ነው። በመሐል ከደብረዘይት ከመጣ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገናል። በክፍል እና በሜዳ ቡድኑ ላይ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል ሞክረናል። በአጠቃላይ ዝግጅታችን የተሳላ ነው። ለእሁዱም ጨዋታ በሚገባ ተዘጋጅተናል።”

ከጋዜጠኞች የቡድኑን ድክመት በተመለከተ ጥያቄ የተሳላቸው አሠልጣኙ “ሙሉ ሆኖ የሚሄድ ቡድን የለም።” ብለው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ የህዝብ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥሪ አስተላልፈዋል። በማስከተል ደግሞ ተጋጣሚያቸው ጋናን በተመለከተ “የጋናን ቡድን በቪዲዮ አይቻለው። ከዩጋንዳ ጋር የተጫወተውን 2 ጨዋታ። እኔ ብቻ ሳልሆን ከተጫዋቾቹም ጋር አይተናል። ቡድኑ ያለው ስም ምንም እንዳያስፈራቸው ተነጋግረን ሜዳ ላይ ያለው ነገር ብቻ ውጤቱን እንደሚለይ ተማምነናል።” ብለዋል።

አሠልጣኙ ጨምረው ቱሪስት ለማ፣ ረድኤት አስረሳኸኝ፣ ገነት ኃይሉ እና መዐድን ሳህሉ ጉዳት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው መዐድን በአንፃራዊነት ለውጥ እያሳየች እንደሆነ ተናግረዋል። የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣቲ ረድኤት ግን ዛሬም ልምምድ አቋርጣ መውጣቷን አመላክተዋል። አሠልጣኙ ምንም ቢሆን ግን እስከ እሁድ 10 ሰዓት የህክምና ባለሙያዎችን እንደሚጠብቁ በመናገር ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

የፅሕፈት ቤት ሀላፊው መድረኩን ተረክበው የካፍን የኮቪድ ፕሮቶኮል በጠበቀ ሁኔታ ደጋፊዎች ስታዲየም ገብተው ቡድኑን እንዲያበረታቱ እንደ አሠልጣኙ ጥሪ አቅርበዋል። ምንም እንኳን ካፍ እስካሁን በዝግ ስታዲየም እንዲደረግ ቢልም ከ15 ቀናት በፊት ንግግሮች መደረግ ጀምረው ስታዲየሙ ከሚችለው ሙሉ አቅም 25 በመቶ እንደተፈቀደ አስረድተዋል። ከአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ጋር በተገናኘ “የአቋም መለኪያ ጨዋታ ቢመቻች መልካም ነው። ይጠቅማል። ይሄንን በወንዶቹ ተመልክተናል። ጊዜው ረዘም ቢልም ሴቶቹ ላይ ሞክረናል። አሁን በቅርበት ልናገኝ የምንችለው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ነው። ከእነሱ ጋር ደግሞ ተጫውተናል። ከዚህ ውጪ ከሞሮኮ ጋር ጨዋታ ልናደርግ ነበር። ግን ሞሮኮ እንድንጫወት የፈለገችው ከጋና ጋር በምንጫወትበት ቀን ነው። ይሄንን ተከትሎ ጨዋታው አልተሳካም።” ብለዋል።

በመጨረሻም ስታዲየም ከሚገቡ ደጋፊዎች ውጪ ያሉ የስፖርት ቤተሰቦች ጨዋታውን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማኅበራዊ ገፆች እንዲሁም በኢቢኤስ ሲኒማ እና ፌስ ቡክ ገፅ በቀጥታ መከታተል እንደሚችሉ ተመላክቷል።