​ኮንጓዊ አማካይ ሲዳማ ቡናን ለመቀላቀል ተስማማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ሲዳማ ቡና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜግነት ያለውን የተከላካይ አማካይ ወደ ክለቡ ለመቀላቀል ስምምነት ፈፅሟል።                                

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እየተመራ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ጥቂት ጨዋታዎች አጀማመሩ ያላማረው እና የኋላ ኋላ ራሱን በደንብ አሻሽሎ በ25 ነጥቦች 5ተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ዙሩን የፈፀመው ክለቡ ለሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ራሱን ለማጠናከር አዳዲስ ተጫዋቾች ማምጣት ጀምሯል፡፡

በዚህም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜግነት ያለውን የተከላካይ አማካይ ኤዲ ኢሞሞ ኒጎዬን እስከ አመቱ መጨረሻ የግሉ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣቱን በተለይ የተጫዋቹ ወኪል አዛርያስ ተስፋፅዮን እና ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል ፡፡
በትውልድ ሀገሩ ክለቦች ሻርክስ ዢ እና ኤ ኤስ ካቫሻ ለተባሉ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው እና በመቀጠል ለቱኒዚያው ዩ ኤስ ሞናስትሪ ከዛም ለግብፁ ሶሞሀ እንዲሁም ያለፉትን አመታት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለኤ ኤስ ቪታ ክለብ ሲጫወት ቆይቶ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከትላንት በስቲያ የመጣ ሲሆን ክለቡ በቀድሞው የህክምና ባለሙያ አበባው በለጠ ጉዳይ በመታገዱ ተጫዋቹ ዛሬ ለመፈረም ወደ ፌዴሬሽኑ ቢያቀናም ውሉ መፅደቅ ሳይችል ቀርቷል፡፡ እግዱ ተነስቶ ተጫዋቹ ውሉ ከፀደቀ በኋላ ከብርሀኑ አሻሞ እና ሙሉዓለም መስፍን ጋር ለቋሚ ተሰላፊነት የሚፎካከርም ይሆናል፡፡

በተያያዘ አዳዲስ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ማምጣት የጀመረው ሲዳማ ቡና በተቃራኒው ከነባር ተጫዋቾች ጋር እንደሚለያይ ይጠበቃል፡፡