[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ14ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ነቀምት ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ደቡብ ፖሊስን ባለ ድል አድርጓል፡፡
ረፋድ ላይ ደቡብ ፖሊስ እና ሶዶ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ግብ ከመቆጠሩ ውጪ ለዕይታ ማራኪ ነበረ ማለት አይቻልም፡፡ ደቡብ ፖሊስ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት በጨዋታው ላይ ማሳየት ቢችልም በመከላከሉ ረገድ ሶዶ ከተማዎች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ፖሊሶች በ15ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ታምሬ ከርቀት ሞክሮ አቡሽ አበበ ባዳነበት አጋጣሚ ወደ ሳጥን መጠጋት የጀመሩ ሲሆን ሶዶዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የተዋጣላቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ የአጨዋወት መንገድ በቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ አላዛር ፋሲካ ግብ ለማግኘት ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርጉም ታይቷል፡፡ ደቡብ ፖሊሶች በአንፃሩ የአጨራረስ ድክመት ነበረባቸው እንጂ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በተደጋጋሚ ደርሰዋል፡፡
ከእረፍት መልስ በተደራጀ የጨዋታ ቅርፅ ወደ ሜዳ የገቡት የአሰልጣኝ አላዛር መለሰው ደቡብ ፓሊሶች ሲሆኑ በአንፃሩ ሶዶ ከተማዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መከላከሉ ትኩረት አድርገዋል፡፡ መሐል ሜዳ ላይ ልዩነት ፈጣሪ በሆነው ብሩክ ዳንኤል ታግዘው ብልጫ የወሰዱት ፓሊሶች 74ተኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ኤልያስ እንድሪያስ ላይ የሶዶው ተከላካይ ዘርአይ ዘነበ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ዳንኤል አስቆጥሮ ደቡብ ፓሊስ 1ለ0 አሸናፊ ሆኗል፡፡
ከሰዓት 8፡00 ሰዓት በፈጣን ሽግግር ረጃጅም ኳስን ለአጥቂዎች በመላክ የሚታወቁት ነቀምቶች ገና በጊዜ ፌድራል ፓሊስን በደንብ በመፈተን በግድ እንዲከላከሉ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በዚህ አጨዋወት በመጀመሪያው አጋማሽ የተቃራኒ ግብ ክልል ደርሰው ነቀምቶች የሞከሩት ኳስ በተከላካይ ተደርቦ የማዕዘን ምት ሲሆን አምበሉ ቴዎድሮስ መንገሻ አሻምቶ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ የአሰልጣኝ ተስፋዬ ፈጠነው ፌድራል ፖሊስ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክርም ሳይሳካላቸው አጋማሹ በነቀምት መሪነት ተገባዷል፡፡
ከእረፍት መልስ አሁንም በረጃጅም ኳስ የተለዩ የነበሩት ነቀምቶች ፌድራል ፖሊስ ላይ የተሻለ ብልጫን በመውሰድ ሁለተኛ ጎላቸውን ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ በዚህም 70ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል ታደለ ሳጥን ውስጥ ከቀኝ በኩል ሰብሮ ገብቶ የቀነሰውን ኳስ አማካዩ ዘሪሁን ይልማ በቀጥታ ሞክሯት ግብ ጠባቂው አሸብር ተስፋዬ ሲተፋት የተመለሰችሁን ኳስ በቅርብ የነበረው ኢብሳ በፍቃዱ ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ውብሸት ሥዩም ከጥልቀት የቅብብሎሽ ሂደት ያገኘውን ኳስ ተቀይሮ ለገባው ዳንኤል ዳዊት አቀብሎት ዳንኤልም ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ማራኪ ጎል በማስቆጠር ጨዋታውን ነቀምት 3ለ0 አሸናፊ እንዲሆን አድርጓል፡፡
10፡00 ሰዓት ላይ ነቀምትን በደረጃ ሰንጠረዡ እግር በእግር የሚከተለው ኢትዮጵያ መድን ከአቃቂ ቃሊቲ ጋር ያደረገው ጨዋታ ተከናውኗል፡፡ በዚህ ጨዋታ በፈጠነ ሂደት ጎል የተመለከትነው በ2ተኛው ደቂቃ ነበረ፡፡ ቻላቸው መንበሩ ከቀኝ በኩል በፍጥነት ጉልበቱን ተጠቅሞ ኳስ እየገፋ ተጫዋቾችን ከቀነሰ በኋላ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ በሀይሉ ኃይለማርያም ኳሷን ሲቆጣጠር እንደምንም ከተከላካይ ጀርባ የነበረው ያሬድ ዳርዛ አግኝቷት ወደ ጎልነት ለውጧታል፡፡ አቃቂዎች ተደጋጋሚ ሙከራ ለማድረግ ቢጥሩም ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል፡፡ 21ኛ ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ ከቀኝ በኩል አክርሮ የመታት ኳስ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ሀብታሙ ሲተፋት አጠገቡ የነበረው ያሬድ ዳርዛ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የመድንን መሪነት አስፍቷል፡፡ ጎል ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የጣሩት አቃቂዎች 44ኛ ደቂቃ ከማዕዘን ምት ጉልላት ተሾመ አስቆጥሮ ጨዋታውን 2ለ1 አድርጓል፡፡
ከእረፍት መልስ በርካታ ቢጫ ካርዶች እና ጭቅጭቆች የታዩ ሲሆን ሰአት ሲያመክን የነበረው የመድኑ ግብ ጠባቂ ጆርጅ ደስታ በሁለት ቢጫ በቀይ የወጣበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡ ብዙም የተለየ ነገር ያላየንበት አጋማሹም በመድን 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።