[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከዚህ ቀደም ከሲዳማ፣ ኦሮሚያ እና አፋር እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ትጥቅ አምራች ከደቡብ ክልል ጋርም የአጋርነት ውል አስሯል።
የኢትዮጵያን እግርኳስ ለዐይን ምቹ በሆኑ እንዲሁም በጥራታቸው ወደር በማይገኝላቸው ምርቶቹ እያደመቀ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ በሁለቱም ፆታዎች ከሚገኙ የፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ እና አንደኛ ሊግ እንዲሁም ከበርካታ የጤና ቡድኖች ጋር መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከክለቦች እና ቡድኖች በተጨማሪም ከሲዳማ፣ ኦሮሚያ እና አፋር እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈፅሞ ስራዎችን እየከወነ ይገኛል። አሁን ደግሞ ከደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት ፈፅሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በሚቆየው ስምምነት ጎፈሬ በክልሉ ለሚገኙ የወረዳ እና የዞን ክለቦች ትጥቆችን የሚያቀርብ ይሆናል። በዋናነት ደግሞ ክለቦቹ ባህል፣ ወግ እና ትሁፊታቸውን በሚገልፅ ሁኔታ ትጥቆቹ እንደሚሰራላቸው በስምምነቱ ተካቷል።
ከዚህ ውጪ ተቋሙ በክልሉ ያለውን የእግርኳስ ሂደት ለማሳደግ የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ይሆናል። በተጨማሪም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ሁነቶች በክልሉ አስተናጋጅነት ሲከወኑ ጎፈሬ የማሰናዳቱን ድርሻ በመውሰድ ክንውኖችን እንደሚያሳምር ተጠቁሟል።