የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 14ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ የ14ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ነገሌ አርሲ ከ ጌዴኦ ዲላ እንዲሁም ገላን ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ የአቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በስምንት ሰዓት የተካሄደው የነገሌ አርሲ እና የጌዴኦ ዲላ ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተፈፅሟል። ሁለቱም ቡድኖች በጥንቃቄ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ማሰባቸው በመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የሚባሉ የጎል ዕድሎችን እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ በ36ኛው ደቂቃ መሐል ሜዳ ላይ ኳሱን በመቆጣጠር ብልጫ የነበራቸው ጌዴኦዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድን ተጫዋች የነበረው አቤኔዘር ሕዝቄል ከግራ መስመር በቀጥታ ወደ ጎል የመታው እና ግብ ጠባቂው እንደምንም ወደ ውጪ ያወጣበት አጋጣሚ የፈዘዘውን ጨዋታ ወደ መነቃቃት እንዲቀየር አድርጓል።

 

ከደቂቃዎች በኋላ በ39ኛው ደቂቃ በነገሌዎች ተከላካይ ሳጥን ውስጥ ተደርቦ የተመለሰውን ጨረቃዋ ላይ የነበረው የጌዴኦው ናትናኤል ሰለሞን በጥሩ ሁኔታ ኳሱን በመቆጣጠር በግራ እግሩ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ግብ ጠባቂው ባጠበበት ቦታ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጌዴኦ ዲላዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከወትሮው ከሚታወቁበት ፈጣን እንቅስቃሴ ተዳክመው የቀረቡት ነገሌ አርሲዎች ባደረጉት ሙከራ በአንድ አጋጣሚ 43ኛው ደቂቃ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ኤፍሬም አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

 

በሁለተኛው አጋማሽ ከጅማሮው አንስቶ ጎል ፍለጋ ሲታትሩ የቆዩት ነገሌዎች ጥረታቸው ብዙም ሳይቆይ ተሳክቶ አቻ የሆኑበትን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ጫላ ተስፋዬ 48ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ጎል አስገኝቷል። በጌዴኦ የሜዳ ክፍል ነገሌዎች በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት በተሻለ ፍላጎት ሲንቀሳቀሱ ያስተዋልን ሲሆን 57ኛው ደቂቃ አቤል ፈንታ ከርቀት የመታውን ግብጠባቂው አድኖባቸዋል። በአንፃሩ ጌዴኦ ዲላዎች በመልሶ ማጥቃት የነገሌዎችን ተከላካዮችን ሲፈትኑ ቆይተው በዚህ ሂደት ውስጥ ናትናኤልን ሰለሞን አሻግሮት ወደ ጎልነት የሚቀየርበትን አጋጣሚ ሙሉዓለም በየነ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ብዙም ሳይቆይ ከመስመር የተጣለለትን ክንዴ አቡቹ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወጥቶበታል።


እየተዳከሙ በመሄድ ባልተደራጀ መልኩ በረጃጅም ኳሶች ነገሌዎች ጎል ለማግባት ያደረጉት ሙከራ ያልተሳካ ሆኖ በጌዴኦ ዲላዎች ተከላካይ እየተመለሰ በራሳቸው ላይ አደጋ ይፈጠር ነበር። ለዚህም በመጨረሻው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ አንስቶ የዕለቱ ኮከብ ተጫዋች ናትናኤል ብቻውን ከግራ መስመር ወደ ሳጥን በመግባት ጎል አገባ ሲባል ሚዛኑን ስቶ ያልተጠቀመበት የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ ነበር። በመጨረሻም የነገሌ አርሲው ምክትል አሰልጣኝ በሽር አብደላ በዕለቱ ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ላይ አላስፈላጊ ድርጊት በመፈፀማቸው በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደው ጨዋታው አንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ነገሌዎች ምድቡን ሊመሩ የሚችሉበትን አጋጣሚ አጥተዋል።

የአስራ አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የገላን ከተማ እና የሀላባ ከተማ ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተገባዷል።

ተመልካችን ያዝናና ሳቢ እግርኳስ ባስመለከተን በዚህ ጨዋታ በሁለቱም በኩል በቅብብሎች አስከፍተው ጎል ለማስቆጠር ሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማራኪ የነበረ ቢሆንም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ቅብብሎሹ እየተቋረጠ ጥቂት የሚባሉ ሙከራዎችን በመጀመርያው አጋማሽ እንድንመለከት አድርጎናል።

በሀላባዎች በኩል በ18ኛው ደቂቃ ሰዒድ ግርማ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂው ያዳነው እና ይህ ኳስ ቀጥሎ ከግራ መስመር ተሻግሮ ጃፋር ከድር በግንባሩ የገጨውን የገላኑ ግብ ጠባቂ ውብሸት ጭላሎ በድጋሚ ያዳነው የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። በአንፃሩ በገላኖች በኩል አጥቂው የኋላሸት ፍቃዱ ተሻጋሪ ኳስ አግኝቶ ደገፍ በማድረግ የመታው ለጥቂት ወጥቶበታል። ወደ ዕረፍት መዳረሻ 45ኛው ደቂቃ ላይ ሀላባዎች በሙሉቀን ተሾመ አማካኝነት ነፃ የጎል ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።


ከዕረፍት መልስ ጎል ፍለጋ ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ገላኖች በየኋላሸት አማካኝነት 55ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረዋል። ለዚህችም ጎል መቆጠር የኢዮኤል ሳሙኤል አስተዋፆኦ የጎላ ነበር። ከጎሏ መቆጠር በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ዕረፍት አልባ ሆኖ ጠንካራ ፉክክር እያስመለከተን ዘለቆ በ65ኛው ደቂቃ ሀላባዎች አቻ የሚሆኑበት አጋጣሚ ከርቀት ፍራኦል መንግሥቱ በግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ በመታው ኳስ ቢፈጥሩም ግብ ጠባቂው አውጥቶበታል።

ሳቢነቱ በቀጠለው በዚህ ጨዋታ የሀላባው ግብጠባቂ የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት የሰራውን ስህተት ተከትሎ የገላኑ አማካይ አፍቅሮት ሰለሞን ነፃ ኳስ አግኝቶ አገባው ሲባል ተከላካዮቹ ተደርበው ያወጡት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር። ይህ ኳስ ወደ ሀላባ የማጥቃት ሽግግር ገብቶ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን የገላኑ ግብ ጠባቂ የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት አርቃለው ያለው ኳስ በማጠሩ ተቀይሮ የገባው የቀድሞ የመከላከያ ፣ የሀዋሳ እና ኤሌክትሪክ ተጫዋች ማናዬ ፋንቱ ወደ ጎልነት በመቀየር ሀላባን አቻ አድርጓል።

በቀሩትም ደቂቃዎች ክፍት ሆኖ በተደጋጋሚ በፍጥነት በሚሄዱ ኳሶች ተመልካችን ቁጭ ብድግ እያደረገ በቀጠለው የዕለቱ አዝናኝ ጨዋታ ገላኖች በኋላሸት ፍቃዱ ሀላባዎች በማናዬ ፋኑት አማካኝነት መሪ መሆን የሚችሉባቸው የጎል ዕድሎች ቢፈጠሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።