ሪፖርት | ጋና ከሜዳዋ ውጪ ኢትዮጵያን አሸንፋለች

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚደረገው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በመጨረሻ ዙር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጋና 3-0 ተሸንፏል፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከመጨረሻው የታንዛኒያ ጨዋታ አሰላለፍ ውስጥ ጉዳት ላይ ያለችው ረድኤት አስረሳኸኝን በአረጋሽ ካልሳ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

10፡00 ሰዓት ሲል በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ተጋጣሚዎቹ ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድን መርጠው ታይተዋል፡፡ለዚህም ማሳያ የሚሆነው መሀል ሜዳ ላይ በተገደበ የጨዋታ አካሄድን ለአስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች መከተላቸው ነው። የመጀመሪያውን የግብ አጋጣሚ መመልከት የቻልነውም 18ኛው ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል አሪያት ኦዶንግ እና ቱሪስት ለማ በፈጠሩት ቅንጅት ቱሪስት ለአረጋሽ ካልሳ ሰጥታት የመስመር አጥቂዋ ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርጋለች።

የጨዋታውን ሚዛን ወደ ሁለቱ ኮሪደሮች በመለወጥ ወደ ማጥቃት ሽግግሩ የገቡት ጋናዎች በሂደት ኢትዮጵያዊያን እንሰቶች የሚሰሩትን የመከላከል ስህተት ለመጠቀም ሲታትሩ ተስተውሏል፡፡ ግሬስ አኒማ የአሰልጣኝ ፍሬው ልጆች በተዘናጉበት ወቅት ከሳጥን ውጪ አክርራ መትታ የላይኛው የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰባት ቀዳሚ ሙካራቸው ሆኗል፡፡ ተሻጋሪ ኳስ አዋጭ ሆኖ የታያቸው ጋናዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ምት ሲገቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ወደ አረጋሽ ካልሳ ባደላ መልኩ መንቀሳቀስን መርጧል፡፡ በዚህ ሂደት 25ኛው ደቂቃ ላይ በማራኪ የቅብብል ሂደት ብዙአየው ታደሰ ለመሳይ አቀብላ አማካዩዋ ለአረጋሽ ሰጥታት በቀጥታ ወደ ጎል ስትልከው ቱሪስት ለማ መትታው እንምንም ጋናዎች ተረባርበው አውጥተውታል፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ ጫናዎች ማሳደር የጀመሩት ጋናዎች 27ኛው ደቂቃ ላይ የተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ሳላማቱ አብዱላሂ ከመረብ ባሳረፈችው ግብ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡

የአሪያት ኦዶንግን ተደጋጋሚ የሜዳ ላይ ስህተትን በመመልከት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ማዕድን ሳህሉን ለውጠው ወደ ሜዳ አስገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ በአረጋሽ ፣ መሳይ እና ገነት አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩሞ ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 38ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሳላማቱ አብዱላሂ ከአርባ ሜትር በላይ እየገፋች ተጫዋቾችን አልፋ ለራሷ እና ለሀገሯ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ አዋህዳለች፡፡ ከሁለተኛው ጎል በኋላ መሳይ ተመስገን ከሳጥን ጠርዝ አክርራ ስትመታ ተከላካዩዋ ሊዊሳ አኒማ በግንባር ራሷ ላይ ለማስቆጠር ተቃርባ የነበረ ቢሆንም በፍጥነት ኳሱን ጋናዎች አስጀምረው ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ሁለት ደቂቃ ሲቀር ሲሲኒያ ኒያማ ከሳጥን ውጪ ኳስ እና መረብን አገናኝታ ጋናን የ3-0 መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ መጫወት ሲችል ጋናዎች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሯቸውን ሦስት ጎሎች አስጠብቆ ለመውጣት በሚመስል መልኩ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ወደ ኋላ መስመራቸው ሸሸት ብለው ሲጫወቱ ብናይም በቅብብል ስህተት ከሚገኙ አጋጣሚዎች ዕድሎችን ከመፍጠር አልቦዘኑም፡፡ ሜዳ ላይ ሳቢ እግርኳስን ሲጫወቱ የታዩት ኢትዮጵያዊያኑ 60ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ኝቦኝ የኝ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ መሳይ ተመስገን ከግራ የጋና የግብ ክልል በቀጥታ መትታ ግብ ጠባቂዋ ኮንላን ሲንቲያን እንድምንም አውጥባታለች፡፡

ገነት ኃይሉን በማስወጣት ይበልጥ መሀል ሜዳውን ለመጠቀም ያሰቡ ይመስሉ የነበሩት ኢትዮጵያዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ ትግልን ሲያደርጉ ታይቷል፡፡ 73ኛው ደቂቃ ላይ እፀገነት ከመሳይ ጋር የፈጠረችውን ስብጥር ተከትሎ መሳይ ለቱሪስት ሰጥታት ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂ ጋር ብትገናኝም የአጥቂዋን መከራ ኮንላን ሲንቲያ በቀላሉ ልትይዝባት ችላለች፡፡ ኳስ ላይ መሠረቱን ያደረገ የአንድ ሁለት የጨዋታ ሂደትን በአሰልጣኝ ፍሬው የሚመራው ቡድን ማሳት ቢችልም የመጨረሻ ውሳኔያቸው ፍፁም ደካማ ሆኖ ታይቷል። በተለይ 85ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን በግቡ ትይዩ ሆና ሳትጠቀም የቀረችበት የመጨረሻዋ አስቆጪ ዕድል ሆና ጨዋታው በጋና 3-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ የሆኑት አምባሳደር መስፍን ቸርነት ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳይያስ ጁራ እና ሌሎች የሥራ አስፈፃሚ ሆሚቴ አባላት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ቡድኑን ሲያበረታቱ ታይቷል።

ያጋሩ