“እነሱም አላለፉም እኛም አልወደቅንም” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በጋና አቻው 3-0 ከተሸነፈ በኋላ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ወደ ኮስታሪካ ለማቅናት የመጨረሻ የደርሶ መልስ ጨዋታውን ቀዳሚ መርሐ ግብር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሰፊ ልዩነት ተሸንፏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ለቀረቡላቸው ሦስት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው

“ጨዋታውን እንደማንኛውም ቡድን ለማሸነፍ ነው የገባነው ፤ የተፈጠረው ነገር ግን ይህ አይደለም። በእግርኳስ ይከሰታል ፤ በጠበቅነው ልክ አይደለም። ጋናም ይህን ያህል ከባድ ቡድን ሆኖ አይደለም እውነት ለመናገር። በእግርኳስ ትልቅም ተሳሳትክ ትንሽም ግብ ከተቆጠረብህ ብልጫ ይወሰድብሀል። ያንን ነው ያየሁት ፤ እኛም ደግሞ የተሻሉ ዕድሎችን አግኝተን ነበር። አለመጠቀማችን እነሱን እንዲነሳሱ አድርጓል። እዛ እየሳትን ነው እዚህ ይገባ የነበረው ፤ ይህ ደግሞ የሚታረም ነገር ነው። ቡድኑም የ20 ዓመት በታች ቡድን መሆኑ እንዳይዘነጋ። ልጆች ናቸው ፤ በዚህ ደረጃም ደርሰው አያውቁም። ልምዱ ቢኖራቸው ደግሞ የተሻለ ነገር ይሰሩ ነበር። በቀጣይ ብዙ የምናስተካክላቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።

የረድኤት አስረሳኸኝ አለመሰለፍ ስለፈጠረው ክፍተት

“ምንም ጥያቄ የለውም ረድኤት ጨራሽ የምትባል አጥቂ ነች። እግርኳስ ተጫዋች ደግሞ ብዙ ጉዳቶች ይገጥሙታል ፤ ያው ተጎድታ ነው ያልተሳተፈችው። የገቡትም ልጆች ደግሞ አቅማቸው የፈቀደውን ነገር አድርገዋል። ቡድኑ በአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን በሁሉም ተጫዋቾች የሚንቀሳቀስ ስለሆነ በቀጣይ ስህተታችንን አርመን እንመጣለን። በግለሰብ ቆሞ የሚሄድ ሳይሆን እንደቡድን የሚንቀሳቀስ ስለሆነ ችግር የለብንም።

ቡድኑ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር የወደጅነት ጨዋታ አለመደረጉ ስለፈጠረው ተፅዕኖ

“ሁሌም እበልጣለሁ ብለህ ልትበለጥ ትችላለህ በእግርኳስ። የግድ ምዕራብ አፍሪካ ፣ ምስራቅ አፍሪካ የሚለው ላይ አይደለም ትኩረት መደረግ ያለበት። ማንም ሰርቶ ከመጣ ሜዳ ላይ ይበልጥሀል። የተወሰኑ ልጆች ጉዳት ነበረባቸው እነ ቱሪስት ለማ እና ገነት ኃይሉ ከጉዳት ጋር ቆይተው እንደምንም አድርሰን ነው። ቡድኑ ሙሉ ሆኖ በጤና ቢመጣ የተሻለ ነበር ብዬ አስባለሁ። እሱም አንድ ክፍተት ነው። እነጋና በወረቀትም በምንም የተሻሉ ናቸው ያ ወደ ኋላ አያደርገንም። ዕድሎችን አግኝታናል ፤ መጠቀም ነው ያልቻልነው። ይሄ ደግሞ የምናርመው ነገር ነው። ቅድም እንዳልኩት እነዚህ ልጆች ከየት ነው የታገኙት የሚለው ከግምት መግባት አለበት። እስካሁን የመጣንበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ነው በቀጣይ ደግሞ እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ። ይሄ ደግሞ ያለቀ ጨዋታ አይደለም። እነሱም አላለፉም እኛም አልወደቅንም።”