የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ መርሐ-ግብሮች አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ዲቻ አቻ ሲለያዩ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ድል ቀንቷቸዋል ።

አርባምንጭ ከተማ 1 – 1 ወላይታ ድቻ

4:00 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማን ከ ወላይታ ድቻ ያገናኛው ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ገና በሦስተኛው ደቂቃ በሀሰን ዘለቀ አማካኝነት ግብ ማገኘት የቻሉት ድቻዎች ግብ ካገኙ በኋላ ቀዝቀዝ ማለት የታየባቸው ሲሆን በተቃራኒው ይበልጥ ጫና የፈጠሩት አርባምንጮች 42ተኛው ደቂቃ ላይ ይድነቃቸው ያሲን ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በጭንቅላቱ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሯት አቻ ሆነዋል። ከእረፍት መልስ አሰልች በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አስደንጋጭ ሙከራ አልነበረውም። ጨዋታውም ከእረፍት በፊት በተቆጠሩት ሁለት ግቦች በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዲያ ሆሳዕና 1 – 2 ሲዳማ ቡና

8፡00 ሰዓት ላይ በሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና መካከል የተደረገው ጨዋታ ሲዳማን አሸናፊ ያደረገ ሲሆን ቡድኑም መሪነቱን አጠናክሯል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም ለተመልካች ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የረባ መከራ ሳያደርጉ ወደ እረፍት ያመሩት ሲሆን ከእረፍት መልስ ግን ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ሲዳማዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ወንድማገኝ ቆልቻ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ከመረብ ጋር ለማዋሐድ ሞክሮ ግብ
ጠባቂ ያወጣበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር። በወጣው ኳስ ምክንያት የተገኘውን የመዓዘን ምት ደግሞ በፍቅር ግዛቸው በድጋሜ በጭንቅላት በመግጨት ቆንጆ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው መሪ አግኝቷል።

ጨዋታው ላይ ይበልጥ የተነቃቁት ሲዳማዎች በድጋሜ 57ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከፍፁም አብርሃም የተሻገረለትን ኳስ በፍቅር ግዛቸው ወደ ግብ ቀይሮ መሪነታቸውን አሳድገዋል። ሲዳማዎች ሁለተኛ ግብ ካገኙ በኋላ የተቀዛቀዙ ሲሆን ሁሌም ግብ ከገባበት በኋላ የሚነቃቃው ሀድያ ሆሳዕና 68ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት ዓለሙ ባስቆጠረው ግብ ይበልጥ ወደ ጨዋታው የተመለሰ መስሎ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በሲዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሰበታ ከተማ 0 – 1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

10:00 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ሰበታን 1 – 0 አሸንፏል። ተመጣጣኝ በነበረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ደካማ የማጥቃጥ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ከእረፍት በፊትም ሆነ በኋላ ደህና የግብ ሙከራ አልተደረገበትም። ከእረፍት በኋላ ተቀይሮ የገባው መልካሙ ክንዱ ግን ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በመልሶ ማጥቃት ግብ አስቆጥሮ ኤሌክትሪክ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

ያጋሩ