[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በክፍል አንድ ጥንክራችን ከዓምና ዘንድሮ የውጤት መንሸራተት ያጋጠማቸው ክለቦች ቁጥሮችን መነሻ በማድረግ በስፋት የተመለከትን ሲሆን አሁን ደግሞ በተቃራኒው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦችን ለመቃኘት እንሞክራለን።
ሊጉን ዘንድሮ ከተቀላቀሉ ሦስት ክለቦች ውጪ ከፍተኛ የውጤት መሻሻል ያስመዘገበው ክለብ አዳማ ከተማ ነው። ዓምና በ15 ጨዋታዎች 7 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ 12 ጨዋታዎችን ተሸንፎ 30 ግቦችን በማስተናገድ በ18 የግብ ዕዳ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጦ የነበረው ክለቡ ዘንድሮ በ14 ነጥቦች ልቆ 21 ነጥቦችን በመያዝ በሊጉ ሁለተኛው ዝቅተኛ ጨዋታዎችን የተሸነፈ ቡድን በመሆን (ከሲዳማ ቡና ጋር ዕኩል 2) ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ዓምና በአሠልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እና ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ 15ቱን ጨዋታዎች ያከናወነው አዳማ ዋነኛ ችግሩ ግቦችን ማስተናገድ ነበር። ከ15ቱ ጨዋታዎችም አንዱ ላይ ብቻ ነበር ግብ ሳያስተናግድ ወጥቶ የነበረው። በዚህም የሊጉ ከፍተኛ ግቦችን ያስተናገደ ቡድን ሆኖ ነበር። የዘንድሮ አዳማ ከተማ ግን ከዓምናው በተለየ ግቡ በቀላሉ የማይገኝ ሆኖ ቀርቧል። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠልም ሁለተኛው ጥቂት ግብ ያስተናገደ ክለብ መሆን ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዴም ቢሆን ለተጋጣሚ ከአንድ በላይ ግብ እንዲያስቆጥር ፈቅዶ አያውቅም። ይህ የመከላከል ጥንካሬ ከወገብ በላይ አለመደገፉ ነው እንጂ አዳማ አሁን ካለበት ደረጃ ተመንድጎ በተቀመጠ ነበር።
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በሚገባ ራሱን ማጠናከሩ ከዓምናው ስህተቱ እንደተማረ የሚጠቁም ነው። በድምሩ 13 ተጫዋቾችን አስፈርሞ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ክለቡ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የነበረውን የተጫዋች ጥራት ችግር ለማሻሻል ሞክሯል። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃም ከአሠልጣኝ ጀምሮ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት የቡድን ግንባታውን ከመከላከል በመጀመሩ ከላይ እንደገለፅነው ዋጋ አግኝቷል።
እንደጠቀስነው በማጥቃቱ ረገድ ግን መጥፎ የውድድር ዓመት ካሳለፈበት የ2013 የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች እንኳን የተሻለ ግብ ማግኘት አልቻለም። በዚህም ዓምናም 12 ዘንድሮም 12 ግቦችን ነው ያስቆጠረው። ይህ ብቻ ሳይሆን ዓምና በአንድ ጨዋታ አራት ግብ ፣ በሌላ ጨዋታ ሦስት ግብ እንዲሁም ተመሳሳይ በሌላ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ ሲታወስ እና ዘንድሮ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ሦስት በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ብቻ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ (አንዱም በፍፁም ቅጣት ምት የተገኘ ነው) ሲታይ ተሻሽሏል ያልነው ቡድን ከፊት የስልነት ችግር እንዳለበት ያመላክታል።
በአዳማ መሻሻል ውስጥ ያለ ሌላኛው የሚያሳማ ጉዳይ የአቻ ውጤቶች መብዛታቸው ነው። ቡድኑ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 60% የሚሆነውን ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ከምንም አንድ ይሻላል የሚባለው ብሂል እንዳለ ሆኖ ቡድኑ አቻ ከወጣቸው 9 ጨዋታዎች በ4ቱ እየተመራ የነበረ መሆኑ እንዲሁም ድል ካደረጋቸው ጨዋታዎች በአንዱ (ሰበታ ከተማ) በተመሳሳይ እየተመራ መሆኑ የአቻ ውጤቱ ጥሩ እንደሆነ ቢያሳይም ቀድሞ ግብ እያስተናገደ ዳግም አቻ ለመሆን መሯሯጡ ግን ዋጋ ያስከፈለው ዋነኛ ነገር እንደሆነ ይታመናል። በተለይ ቀድሞ ግብ ያስቆጠረው ክለብ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት የሚያደርገውን የመከላለል ጥረት ሰብሮ ለመግባትም ይቸግራል።
ከአዳማ በመቀጠል ከፍተኛ መሻሻል ያሳየው ክለብ ሲዳማ ቡና ነው። ዓምና በመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎች 14 ነጥቦችን ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ከፍ ብሎ የነበረው ሲዳማ ዘንድሮ ከወራጅ ቀጠናው በ11 ነጥቦች እና 9 ደረጃዎች ርቆ 5ኛ ደረጃን ተቆናጧል። በሁለት ጊዜ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ሲዳማ ዘንድሮ ከዓምናው የከፋ አጀማመር ቢያደርግም ቀስ በቀስ ለውጥ በማሳየት ደረጃውን አሻሽሏል። ዓምናው በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደገባ ሲታመን የነበረው ክለብ በመጀመሪያዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ድሎችን ሲያገኝ ዘንድሮ ግን አንዱን ብቻ ነበር ያሸነፈው። ልዩነቱ ዘርዓይ የመሩት ቡድን ከ10 ጨዋታዎች ግማሹን የተሸነፈ ሲሆን የዘንድሮ የገብረመድህን ስብስብ ግን ከ10ሩ ሁለቱን ብቻ ነው የተረታው።
በአብዛኛው በ4-3-1-2 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ የሚጫወተው ሲዳማ የቡድኖች አከርካሪ (Spine) ተደርጎ በሚወሰደው ቦታ ግንባታውን እንዳደረገ ይታመናል። በዚህም መሐል ለመሐል ከግብ ጠባቂው እስከ መጨረሻ አጥቂው የሚሰለፉት ተክለማርያም፣ ያኩቡ፣ ፍሬው እና ይገዙ 15ቱም ጨዋታዎች ላይ የተሳተፉ ብቸኞቹ ተጫዋቾች ናቸው። እነዚህን ተጫዋቾች መነሻ በማድረግ በሚከናወኑት አምስቱም የጨዋታ ምዕራፎች (መከላከል፣ ማጥቃት፣ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግር፣ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር እና የቆመ ኳስ አጠቃቀም) ላይም ከዓምናው በተሻለ ዕድገት አሳይቷል። በዋናነት ደግሞ በቡድናዊ መዋቅር ከኳስ ውጪ መታተር እና ሽግግሮችን በአግባቡ መጠቀም ከዓምናው የተሻለበት ጉዳይ ነው። ከምንም በላይ ግቦችን የማስተናገድ አባዜ ተጠናውቶት የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ መሠረቱን በተሻለ መዋቅር ገንብቶ መምጣቱ ለለውጡ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። ለማሳያ ዓምና 22 ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን ዘንድሮ ግን በ10 ቀንሶ 12 ጎሎችን ብቻ ለተጋጣሚ ሰጥቷል።
ከወገብ በላይ ስልነት ጨምሮ የመጣው ሲዳማ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከረ በሚገኘው ይገዙ ቦጋለ ብቃት እጅጉን እየተጠቀመ ይገኛል። ዓምና በ15ቱ ጨዋታዎች ምንም ጎል አስቆጥሮ በማያውቀው እና በ21 የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ጎል ያገኘው ይገዙ ዘንድሮ የቡድኑን ለግማሽ የተጠጋ ኳስ ከመረብ አዋህዷል። እሱ ብቻ ሳይሆን ዓምና በ15ቱ ጨዋታዎች 2 ግብ ብቻ አስቆጥሮ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝም ዘንድሮ እጥፍ ጎል በስሙ አስመዝግቧል። የሁለቱ አጥቂዎች ምርጥ ብቃት ላይ መገኘት ያለ ጥርጥር ጠቃሚ ቢሆንም ቡድኑ ከእነርሱ ውጪ በክፍት ጨዋታ ኳሶችን የሚያስቆጥርለት እና ጫናዎችን የሚጋራ ተጫዋች የሚፈልግ ይመስላል። በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር ዓምና 5 ተጫዋቾች በክለቡ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ የነበሩ መሆኑ እና ዘንድሮ ስድስት መኖራቸው በግብ ስብጥሩ ረገድ መጠነኛ ዕድገት እንዳለ ቢያሳይም ከይገዙ እና ሀብታሙ 12 ጎሎች ውጪ ከተቆጠሩት አምስት ጎሎች አንዱ ብቻ በክፍት ጨዋታ መሆኑ ጉዳዩን የጎላ ያደርገዋል። በዚህም ፍሬው ሰለሞን ድሬዳዋ ላይ ካስቆጠራት የ75ኛ ደቂቃ ጎል ውጪ ዳዊት ተፈራ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን እንዲሁም ግርማ በቀለ እና ብሩክ ሙሉጌታ ከመዓዘን ምት መነሻን ካደረሱ ኳሶች ያስቆጠሩት ነው። በአጠቃላይ ሲዳማ ግቦችን በማስቆጠር ቢሻሻልም የግብ ምንጮችን በማስፋቱ ረገድ ግን ክፍተት አለበት።
በቡድኑ ዕድገት መጠቀስ ያለባቸው ዋነኛው ሰው ደግሞ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ናቸው። አሠልጣኙ አሁን ብቻ ሳይሆን ዓምናም ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ያሳዩት ለውጥ የማይዘነጋ ሲሆን ዘንድሮም የራሳቸውን የተጫዋቾች ምርጫ በማድረግ ሙሉ የቅድመ ውድድር ዝግጅት አከናውነው ያሳዩት ብቃት ከዓምናው ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ነው። በዋናነት ጨዋታን የማንበብ እና የመለወጥ አንፃራዊ ብቃት ይነሳል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ እየተመራ የጨዋታውን ውጤት ለመገልበጥ እና ለማሸነፍ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ብዙ ጊዜ የተዋጣላቸው ነበሩ። ባህር ዳር እና ሀዲያን ያሸነፉበት መንገድም ለዚህ ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተጫዋቾቻቸው ላይ ያላቸው ትዕግስት እና ዕምነት ዋጋ ከፍሏቸዋል። ለምሳሌ ሀብታሙ ፣ ይገዙ እና ዳዊትን በሚገርም ትዕግስት ወደ ጥሩ ብቃታቸው እንዲመጡ ማድረጋቸው ትልቅ ነገር ነው።
በተገባደደው የሊጉ የመጀመሪያ ዙር አስገራሚ ግስጋሴ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ወላይታ ድቻ ነው። ሽንፈት ካስተናገደበት የመጀመሪያው የድሬዳዋ ጨዋታ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የወልቂጤ ፍልሚያ በውጤት ተኮር አቀራረብ ወደ ሜዳ የሚገባው የአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስብስብ በወረቀት የዋንጫ ተፎካካሪ ተደርገው የታሰቡ ቡድኖችን በመብለጥ ከሊጉ አጋፋሪ በሦስት ነጥብ እና አንድ ደረጃ ብቻ ዝቅ ማለቱ የብዙዎችን ቅንድብ በአግራሞት የሰቀለ ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ለወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ የነበረው ድቻ አሁን ከመሪው በአንድ ደረጃ ብቻ ዝቅ ማለቱ ጉዞው ምን ያህል ዕድገት እንደነበረው ያሳያል። በሁለት የጨዋታ ሳምንታትም (በ5ኛ እና 6ኛ) የሊጉ መሪ ሆኖ 10 ተከታታይ ቀናትን አሳልፏል። ካለው አንፃራዊ ስብስብ ይህ ፍፁም ያልተጠበቀ ሲሆን ከዓምናው የ15 ሳምንታት ጨዋታዎች ውጤት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በሁለት ጨዋታዎች ድል እና በአንድ ጨዋታ አቻ ውጤት በሚገኝ ነጥብ (7) ዘንድሮ ዕድገት አሳይቷል።
ክረምት ላይ አዲስ አሠልጣኝ የቀጠረው ክለቡ የዓምናውን የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች በደለለኝ ደቻሳ እና ዘላለም ሽፈራው ነበር የተመራው። አሠልጣኝ ዘላለም በ9ኛ ሳምንት ቡድኑን ከያዙ በኋላ እስከ 15ኛ ሳምንት ድረስ አንድም ጨዋታ ባይሸነፉም ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ 8 ጨዋታዎች 20 ነጥቦች ጥሎ አጀማሩን የከፋ አድርጎበት ነበር። ከዓምና ዘንድሮ በጦና ንቦቹ ቤት የተሻሻለው ዋነኛ ጉዳይ አልሸነፍ ባይነይ ፣ ታታሪነት እና እንደ ቡድን የመጫወት ነገር ነው። በተለይ ተስፋ ባለመቁረጥ ስሜት ሰበታ እና አዲስ አበባ ላይ ከመመራት ተነስተው እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃ ያገኙት ሦስት ነጥብ ዋጋቸው ከፍ ያለ ነበር። ከዚህ ውጪ ዓምና በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር በስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግዱ ወጥተው በጠቅላላው 17 ግቦችን አስተናግደው የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ በ7 ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ በ8ቱ ብቻ 12 ጎል ገብቶባቸዋል። ከግብ ዘብ ውጪ በኋላ መስመሩ ላይ ዓምናም ዘንድሮም ተመሳሳይ ተጫዋቾችን የሚጠቀመው ወላይታ ድቻ ለዚህ መሻሻሉ ደግሞ ቀድመን የገለፅነው እንደ ቡድን መጫወት መቻሉ እና ከኳስ ውጪ ታታሪ መሆኑ ነው።
ዓምና በ15 ጨዋታዎች 5 ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች (ፀጋዬ ብርሃኑ) የነበረው ድቻ ዘንድሮም ከ5 ግብ በላይ የሚያስቆጥርለት ተጫዋች አላገኘም። ይህ ብቻ ሳይሆን 6ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀበት የ2013 የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች በታች አጠቃላይ ግብ ማስቆጠሩ በመጠኑ የማይዋጥ እውነታ ነው። ተሻሽሏል ባልንበት ዓመት በሦስት ጨዋታዎች ብቻ 2+ ጎሎችን ሲያስቆጥር ዓምና ግን በ5 መርሐ-ግብሮች ሁለት እና ከዛ በላይ ኳሶችን ተቃራኒ መረብ ላይ አሳርፎ ነበር። ሰባት ጨዋታዎችን ደግሞ በአንድ ግብ ልዩነት ብቻ (6ቱን 1ለ0) አሸንፏል። ይህ ከላይ እንደገለፅነው ውጤት ተኮር አጨዋወት መከተሉን በሚገባ የሚያመላክት ሲሆን ከሌሎቹ የሊጉ ቡድኖች በተለየ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ አስጠብቆ መውጣት እንደሚችልም የሚያሳይ ነው። ከዚህም መነሻነት ዘንድሮ ዘጠኝ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሊጉ ቀዳሚው ክለብ ሆኗል (ዓምና 6 ጨዋታዎችን ነበር ያሸነፈው)። እንደ ሲዳማ ቡናው አቻቸው ሁሉ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ቡድኑን የማሻሻል ድርሻ ግን ሳይነሳ አይታለፍም። ከሁሉም በላይ በስብስብ ጥራት እና በተገማችነት ዝቅ ያለ ቦታን ይዞ ያለበቂ ቅድመ ዝግጅት ውድድር ተሳትፎ ዓመቱን የጀመረውን ቡድን ያለውን ጠንካራ ጎን ላይ ተመስርቶ በየጨዋታው ውጤት ይዞ እንዲወጣ ማስቻላቸው የሚያስመሰግናቸው ነው።
እንደ ወላይታ ድቻ ዓምና ካስመዘገበው ውጤት በ7 ነጥቦች ዕድገት ያሳየው ሌላኛው ክለብ ሀዋሳ ከተማ ነው። ዓምና በ15 ጨዋታዎች 20 ነጥቦችን በመያዝ በ1 የግብ ዕዳ 8ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ሀዋሳ ዘንድሮ ሳይጠበቅ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ራሱን ከትቶ ከመሪው በ4 ነጥቦች ብቻ ርቆ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በዘንድሮ የውድድር ዓመት አሠልጣኝ ቀይረው ከመጡ 8 ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት 8 ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም ባለፈው ዓመት አሠልጣኝ ሙሉጌታ የጀመረውን የቡድን ግንባታ በሚያፋልስ መልኩ አሰላለፎችን ሲነካ አልታየም። ከፈረሙት ስምንቱ ተስፉ ኤሊያስ፣ ኤርሚያስ በላይ እና ብሩክ ኤሊያስ በድምሩ 30 ደቂቃዎችን ብቻ ነው ሜዳ ላይ ያሳለፉት። ከቀሪዎቹ አራቱ ደግሞ በቃሉ ገነነ እና መሐመድ ሙንታሪ ከ1 ሺ በላይ ደቂቃዎች በመጫወት አሳልፈዋል። እንዳልነው ይህ በአዲሱ አሠልጣኝ ስርም የቡድኑ ግንባታ በተጫዋቾች መተካካት እንዳልተደነቃቀፈ ያሳያል።
ዘንድሮ በኃይቆቹ ቤት የተለወጠው ዋነኛው ነገር ፍጥነት ነው። በዘመናዊ እግር ኳስ ብዙ ነገሮች በፍጥነት እየተከናወኑ ሲገኝ ሀዋሳም ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ከዓምናው በተሻለ ፍጥነት ጨምሯል። በአክሲዮን ማኅበሩ ይፋዊ መረጃ መሠረት አማካይ የቡድኑ ተጫዋቾች ዕድሜ በ23 እና 24 ዓመት መካከል መሆኑ ሲታወስ ደግሞ አፍላነት ለሚፈልገው ፍጥነት ቡድኑ እንደማይታማ እንረዳለን። ዓምና ካሸነፈው በሁለት በላቀ ቁጥር ድል ያደረገው ሀዋሳ ከወገብ በላይ ያን ያህል ለውጥ ባያሳይም በመከላከሉ ረገድ ያሳየው መሻሻል ከዓምናው በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። ሦስት እና ከዛ በላይ ግቦችንም ሦስት ጊዜ ያስተናገደ ሲሆን ዘንድሮ ግን ከፍተኛ በጨዋታ የተቆጠረበት ጎል ሁለት ብቻ ነው። እንደየተጋጣሚው የሚቃኝ የሦስት እና የአራት ተከላካዮች ጥምረቱም ከአንዳንድ ጨዋታዎች ውጪ በእንቅስቃሴ ረገድ መልካም የሚባል ነበር።
ምናልባት ዓምናም ዘንድሮም ያልተለወጠው ብቸኛ ነገር የሚመስለው የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ነው። ዓምና ከተቆጠሩት 17 ጎሎች 64.7% ያስቆጠሩት መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ዘንድሮም ከ19ኙ የቡድኑ ጎሎች 10ሩን አስቆጥረዋል። የቡድኑ ዋነኛ የግብ ምንጭ የሆኑት ሁለቱ አጥቂዎች በተለይ በመልሶ ማጥቃት እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ወቅት ዋነኛ ብቃታቸው በሆነው ፍጥነት የተጋጣሚን ጥልቀት እያጠቁ ቡድኑን መታደግ መቀጠላቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ በአብዛኛው ዓምናም ሆነ ዘንድሮ የተሸነፉባቸው እና ነጥብ የጣሉባቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ ሲጫወት ማስከፈቻ አማራጭ መፍትሔ እንደሌላቸው የተስተዋለበት ነበር።
በእንቅስቃሴም ሆነ በነጥብ ደረጃ መሻሻል ያሳየው እና የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ አናት ይዞ ዙሩን ያገባደደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በ15ቱ ጨዋታዎች አንድም ጨዋታ አልተረታም። ዓምና ባደረጋቸው የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች በ26 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቡድኑ ከዘንድሮ በተቃራኒ ሦስት ጨዋታዎን ተሸንፎ ነበር። በሰርቢያዊው ዝላትኮ ክራምፖቲች እየተመራ የውድድር ዓመቱን ቢጀምርም የ63 ዓመቱ አወዛጋቢ አሠልጣኝ ከሁለት ጨዋታዎች በላይ ቡድኑን ሳያገለግሉ ቀርተው በምክትል አሠልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ በመመራት አስገራሚ ጉዞን አድርጓል። ከምንም በላይ በስሩ ከሚገኙት ወላይታ ድቻ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ላይ ያገኘው ውድ 9 ነጥብ አናቱን ያለ ከልካይ እንዲቀመጥበት አስችሏል።
በፈረሰኞቹ ቤት ጨዋታዎችን አለመሸነፍ መልካም ቢሆንም ግቦችን አለማስተናገድ ደግሞ ዋነኛ ከዓምና የታየው ዕድገት ነው። ዓምና በ15 ጨዋታዎች 18 ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን ዘንድሮ ግን በሊጉ ዝቅተኛ ግቦችን ያስተናገደ ክለብ በመሆን ከዓምናው 12 ግቦችን በመቀነስ 6 ጊዜ ብቻ መረቡን አስደፍሯል። በዘጠኝ ጨዋታዎችም ግብ ሳይቆጠርበት ወጥቷል። ለዚህ ደግሞ 1349 ደቂቃዎች የተጫወተው ፍሪምፖንግ ሜንሱ እና 1260 ደቂቃዎችን በሜዳ ግልጋሎት የሰጠው ምኞት ደበበ ከግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎ (1260 ደቂቃዎች) ጋር የፈጠሩት ጠጣር የኋላ መስመር ተጠቃሽ ነው። በተለይ በግብ ብረቶቹ መሐል የሚቆመው ሉክዋጎ በፍፁም ቅጣት ምት ከተቆጠሩበት የአዲስዓለም እና ካፓይቶ ጎሎች መካከል ለ687 ደቂቃዎች ግቡን ሳያስደፍር መውጣቱ ዓምና በ15 ጨዋታዎች ሦስት ግብ ጠባቂዎችን ቀይሮ ለነበረው ቡድኑ በቦታው እፎይታን የሰጠ ነው። ከዚህ ውጪ ከጠቀስናቸው ሜን-ምኞ (ሜንሱ እና ምኞት) ጥምረት በተጨማሪ የመስመር ተከላካዮቹ ሔኖክ እና ሱሌይማን ለጠጣሩ የኋላ መስመር አበርክቶ ነበራቸው።
ከወገብ በላይ የቀድሞ ቀጥተኛነቱን እያገኘ የመጣው ጊዮርጊስ እንደ ዓምናው በ15 ጨዋታዎች ሁለት አሐዝ ላይ የደረሰ ጎል ያስቆጠረለት አጥቂ ባለቤት ነው። ዓምና ጌታነህ ከበደ 11 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ቶጓዊው አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ 10 ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል። እርግጥ ቡድኑ ከአጠቃላይ የማጥቃት ቁጥሮች ግቦችን በማስቆጠር ከዓምናው በሦስት ጎሎች የቀነሰ ጎል ዘንድሮ ቢያስቆጥርም በተለየ ሁኔታ ጨዋታዎችን ቶሎ ለመወሰን በጊዜ ግቦችን የማስቆጠር ሂደት ላይ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። በዚህም በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች እንኳን ዓምና ሁለት ጎል (አንዱም በፍፁም ቅጣት ምት) ሲቆጠሩ ዘንድሮ ግን ሰባት ኳሶች ባስቀመጥነው የጊዜ ሰሌዳ ብቻ መረብ ላይ አርፈዋል። ይህ የተጋጣሚን ተነሳሽነት ለማውረድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሲኖረው አልፎ አልፎ ግን በጊዜ ግብ ሳያስቆጥር ሲቀር እየተዳከመ የሚመጣበት ምልክቶችንም አስተውለናል። የሆነው ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ 27 ግቦችን ካስቆጠረበት ዓመት ዕኩል አሁንም በተመሳሳይ በ15ቱ ጨዋታዎች አጎሮን ጨምሮ አስር ጎል አስቆጣሪ ተጫዋቾች ይዟል።
ሌላው በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመግባት አፋፍ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከዓምና የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች ዘንድሮ የሦስት ነጥብ ዕድገት አሳይቷል። እርግጥ መሻሻሉ ጥሩ ቢሆንም ዘንድሮ ስድስት ጨዋታዎች በመቀመጫ ከተማው አከናውኖ አንዱን ብቻ ማሸነፉ ለውጡ ብዙም የሚያመፃድቅ እንዳልሆነ ያመላክታል። ለዚህም ከሌሎቹ ክለቦች በተለየ ገና በግማሽ ዓመት ሦስተኛ አሠልጣኝ በቦታው ሾሟል። ሌላኛው ክለብ ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ የአንድ ነጥብ እምርታ አስመልክቷል። ካስመዘገበው አጠቃላይ ነጥብ በአንድ ብቻ ያነሰ ሽንፈት (10) ያስተናገደው ጅማ በአንፃራዊነት የሚያስተናግዳቸው ጎሎች እንዲሁም በተቃራኒው ያስቆጠራቸው ጎሎች ወረድ ቢሉም ከዓምናው በአንድ የበለጠ ጨዋታ በማሸነፉ አንድ ነጥብ ጨምሯል። ዓምና በሊጉ ከተሳተፉት 13 ክለቦች ዘንድሮ ተመሳሳይ ነጥብ ያገኘው ብቸኛው ክለብ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ነው። ቡድኑ በሁለቱም ዓመት በ15 ጨዋታዎች ዕኩል 20 ነጥቦችን ሰብስቧል።