የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የ15 ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በሼር ሜዳ እየተካሄደ የሚገኘው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ካፋ ቡና ኮልፌ እና ሺንሺቾ ድል ቀንቷቸዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከፋ ቡና ቡታ ጅራ ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

ቡታጅራ ከተማዎች ትጥቅ አሟልተው ባለማቅረባቸው ምክንያት ይጀምራል ተብሎ ከተቀመጠበት ጊዜ በሃያ ደቂቃ ዘግይቶ በጀመረው የካፋ ቡና እና የቡታጅራ ከተማ ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቅ የተስተዋለበትን እንቅስቃሴ አሳይቷል። በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ቡታጅራዎች ቢሆኑም የመጀመርያውን የጎል ዕድል በመፍጠር ቀዳሚ የነበሩት ካፋዎች ነበሩ። ቀኝ መስመር እየተነሳ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ፍጥነቱን በመጠቀም የቡታጅራዎችን ተከላካይ ክፍልን ጫና ውስጥ ሲከት ያረፈደው አምቤነ ዘውዴ በ13ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው አናት ላይ አሳልፎ ቢመታውም ኳሱ ኃይል ያልነበረው በመሆኑ የቡታጅራ ተከላካዮች ወደ ውጪ አውጥተውታል። በረጃጅም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ ይሞክሩ የነበሩት ካፋዎች ጥረታቸው ተሳክቶ በ20ኛው ደቂቃ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የተጣለለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ከተቆጣጠረ በኋላ በግሩም አጨራረስ ይበልጣል አደም ካፋ ቡናዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የካፋን ጎል ያስቆጠረውን አጥቂ ይበልጣል አሰልጣኝ አዲሴ ካሴ በአስገራሚ ሁኔታ ከዕረፍት መልስ ወደ መሐል ተከላካይነት ቀይረው አጫውተውታል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሌላ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ካፋ ቡናዎች ቢያገኙም አምቤነ ዘውዴ ወደ ላይ የሰደደዳት ኳስ የምታስቆጭ ነበረች። የመጫወት ፍላጎታቸው ቀዝቀዝ ብሎ የታየው ቡታጅራዎች ሳይጠበቅ ከውሀ ዕረፍት መልስ በ35ኛው ደቂቃ ወንድማአገኝ አብሬ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነው መጫወት በጀመሩት ካፋ ቡናዎች በኩል በ53ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ሱራፌል ከመስመር የተሻገረለትን በግንባሩ ግጭቶ የመታው ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ቀስ በቀስ ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የቻለው ይህ ጨዋታ የጠራ የግብ ማግባት ዕድል ሳይፈጠርበት ዘልቆ ከውሃ ዕረፍት መልስ ካፋ ቡናዎች መሪ የምታደርጋቸውን ጎል አስቆጠረዋል።

በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ የገባውን ኳስ አበበ ታደሰ ራሱ መጠቀም እየቻለ በተሻለ አቋቋም ለሚገኘው ሱራፌል ፍቃዱ አቀብሎት በቀላሉ ወደ ጎልነት በ75ኛው ደቂቃ ቀይሮት የካፋን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። መምራት የቻሉበትን ጎል ካፋዎች ካስቆጠሩ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ገዛኸኝ ፍቃዱ ተጫዋች በመማታቱ በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። የካፋ ቡድን ላይ ብልጫ እንደመውሰዳቸው ቡታጅራዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው ይጫወታሉ ተብሎ ቢገመትም የካፋ የመከላከል ጥንካሬ መስበር አቅቷቸው ምንም ሳይፈይዱ ጨዋታው በካፋ ቡናዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ስምንት ሰዓት ላይ ሰንዳፋ በኬን ከኮልፌ ቀራኒዮ ያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር አስመልክቶን በኮልፌ 4-3 አሸናፊነት ተገባዷል

ጨዋታውን የጀመሩት ኮልፌዎች አስቀድመው በአራተኛው ደቂቃ ነበር ጎል ማስቆጠር የጀመሩት። የሰንዳፋው በኬ ግብ ጠባቂ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት እሱባለው ሙሉጌታ ወደ ጎልነት ቀይሮት ኮልፌዎች መምራት ቻሉ። ተመጣጣኝ ፉክክር እያስተዋልንበት በቀጠለው በዚህ ጨዋታ 15ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ሰንዳፋ በኬዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ሄኖክ ከበደ በጥሩ ሁኔታ ቢመታውም ግብ ጠባቂው እሸቱ ተሾመ አድኖበታል።

አልፎ አልፎ ኳሱን መስርተው ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ኮልፌዎች ከመስመር በሚሻገሩ እንዲሁም በቀጥተኛ ኳስ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉ ሲሆን የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የሆነ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በ20ኛው ደቂቃ የተጣለለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ግብ ጠባቂውን ተከላካዮችን ጨምሮ በማለፍ እሱባለው ሙሉጌታ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ሰንዳፋዎች ሁለት ጎል ቢቆጠርባቸውም ከእንቅስቃሴ ባለመውጣት ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 38ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ፌሶ ሳንዴቦ በግንባሩ ከመሬት ጋር አንጥሮ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ወደ ዕረፍት መዳረሻ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኮልፌው የመስመር አጥቂ እሱባለው ሙሉጌታ በተመሳሳይ መንገድ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ሐት ሀትሪክ የሚሰራበትን አጋጣሚ ለመጠቀም ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የነበረ ቢሆንም የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት አጋጥሞት ሳይጠቀምበት ተቀይሮ ወጥቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በወጣት ተጫዋቾች የተገነቡ መሆናቸውን ተከትሎ በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ እጅግ ማራኪ የሆነ ጨዋታ አስመልክተውናል። ሰንዳፋ በኬዎች ተጭነው በመጫወት የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቢንቀሳቀሱም እምብዛም ፍሬያማ ሲሆኑ አልነበረም። የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድረግ የሞከሩት ኮልፌዎች በ69ኛው ደቂቃ እሱባለውን ቀይሮ የገባው ባለ ክህሎቱ የግራ እግር ተጫዋቹ አብርሀም አሰፋ በጥሩ አጨራረስ የጎሉን መጠን ወደ ሦስት አድርሷል።

ሦስት ጎሎች ቢቆጠርባቸውም እጅ ሳይሰጡ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲታትሩ የቆዩት ሰንዳፋዎች ለጎሉ ቲዩ አስራ ስድስት ከሀምሳ መስመሩ ላይ ከተሰጣቸው ቅጣት ምት የቡድኑ አንበል ዳኛቸው ብርሀኑ ግሩም ጎል በ72ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። በጎሉ መቆጠር የተነቃቁት ሰንዳፋ በኬዎች ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ቅዱስ ተስፋዬ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ሦስት አቻ አድርጓል። የጨዋታው ግለት በቀሩት ደቂቃዎች ቀጥሎ በ82ኛው ደቂቃ የተሰጠውን የማዕዘን ምት መነሻ ያደረገች ጎል አንበሉ ፈቱ አብደላ በግንባሩ ባስቆጠረው ጎል ኮልፌዎችን የ4-3 ባለድል መሆን ችለዋል።


የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የቂርቆስ እና የሺንሺቾ ጨዋታ በሺንቺቾ 1–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ እጅጉን በተቀዛቀዘ መልኩ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ታይቶበታል፡፡ በመሀል ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ኳሶች ታጅቦ የተካሄደው ይህ የጨዋታ ጉሽሚያዎች የበዙበትም ነበር፡፡ በዚህም በመጀመርያው አጋማሽ የጠራ የጎል አጋጣሚ ሳንመለከት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያስመለክቱንም ሁለቱም ቡድኖች ሦስተኛው የሜዳው ክፍል ሲደርሱ ከሚሰሩት ስህተት መነሻነት እስከ 69ኛው ደቂቃ ጎል መመልከት አልቻልንም ነበር። ቂርቆስ ግብ ጠባቂ የሰራውን ስህተት መነሻ ያደረገች ኳስ ያገኘው ድልነሳው ሺታው ግብ ጠባቂውን በማለፍ ሺንሺቾን መሪ የምታደርግ እና በጨዋታው ብቸኛ የሆነችውን ጎል አስቆጥሯል። በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም በዕለቱ የመስመር ዳኛ ይነሳባቸው የነበሩት ቂርቆሶች በዳኝነቱ ላይ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ተመልክተናል። ውጤቱን ለማስጠበቅ በሙሉ አቅማቸው በራሳቸው የሜዳ ክፍል በዝተው ሲከላከሉ የቆዩት ሺንሺቾዎች ተሳክቶላቸው ውጤቱን አስጠብቀው በ1-0 አሸናፊነት አጠናቀዋል።