[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የዩጋንዳውን የመልስ ጨዋታ የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሕንድ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የ2022 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 2-2 መለያየቱ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ በመጪው እሁድ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከሚደረገው የመልስ ጨዋታ በፊት ዛሬ 09:00 ላይ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ በሰጡት ማብራሪያ መሰረት ብሔራዊ ቡድኑ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 02 ድረስ በቀን ሁለት ጊዜ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህኛው ሳምንት መግቢያ ጀምሮ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም ጨዋታውን በሚያደርግበት የአበበ ቢቂላ ስታዲያም ሲሰራም ነበር። ልምምዱ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ‘ጠንካሮች ፣ ፈጣኖች እና ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ያላቸው’ ብለው የገለጿቸው የዩጋንዳ ተጫዋቾችን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ያማከለ እንደነበርም ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኙ ቡድኑ መሀል ላይ የነበረበትን ድክመት ለማሻሻል ሲስራ መቆየቱን የተናገሩ ሲሆን በእርስ በእርስ ጨዋታዎች እና ከወንድ ቡድኖች ጋር በተደረጉ ጨዋታዎች አቋማቸውን መፈተሻቸውንም ገልፀዋል።
ዩጋንዳ ላይ በነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ ቡድኑ 2-0 ከመመራት ተነስቶ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ያለፈ ጉዳይ ነበር። አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ይህንን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ “ከዚህ ስንሄድ ውጤት ይዞ ለመምጣት ትልቅ ተነሳሽነት ነበረን። ለውድድሩ እንግዳ ብንሆንም አንድ ነገር ነግሬያቸው ነበር። ‘የኢትዮጵያ ህዝብ ከእኛ ብዙ ነገር ይፈልጋል። እስከመጨረሻው ደቂቃ የቻልነውን ነገር መስራት አለብን ፤ እያንዳንዱ ደቂቃ ዋጋ አለው። እስከመጨረሻ ድረስ ዋጋ ከፍለን ውጤት ማምጣት አለብን። ሁለትም ሦስትም አራትም ጎል ሊገባብን ይችላል። ግን ጨዋታ የሚያልቀው ዳኛው በቃ ሲል ነው።’ ብያቸው ነበር። ልጆቹም ደግሞ ያንን ሰምተው ስለገቡ እንዲሁም በባህሪ ጥሩ እና ብዙ ሊሰሩ የሚጥሩ ልጆች በመሆናቸው ጎል ሲገባባቸው የመደናገጥ ነገር አልነበረባቸውም። በመሆኑም እስከመጨረሻው ደቂቃ ተጫውተው ውጤት ይዘው ወጥተዋል።” ብለዋል።
አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ቡድኑን ይዘው ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያድርጉ እንጂ እስካሁን ቋሚ ኮንትራት አልፈረሙም። ሆኖም ግን ፌዴሬሽኑ አምኖባቸው እስካመጣቸው ድረስ ዘላቂ ኮንትራት እንደሚሰጣቸው ያላቸውን ዕምነት በመግለፅ አሁን ላይ ግን ትኩረታቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ላይ መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከዚህ በጨማሪ ባሳለፍነው እሁድ የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ በጋና የደረሰበትን የ 3-0 ሽንፈትን በቦታው ተገኝቶ መከታተሉ ለቡድናቸው ትምህርት እንደሰጠ ሲያስረዱ “የእኛን ቡድን ብቻ ሳይሆን የጋናንም ጭምር ነው ያየነው” በማለት ጀምረው ተጫዋቾቻቸው የሁለቱን ተጋጣሚዎች ጠንካራ እና ደካማ ጎን አይተው ተገቢውን ትምህርት ወስደዋል እንጂ ውጤቱ ተፅዕኖ እንዳልፈጠረባቸው ተናግረዋል።
በዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ በተነሳው ጥያቄ አሰልጣኙ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ኖሮ ከዛ ላይ ተጫዋቾች ቢመርጡ የተሻለ ይሆን እንደነበር አስረድተው አሁን ላይ ግን ካሉት ሊጎች በዕድሜ የሚሆኑትን እና ከአካዳሚ መምረጣቸውን እንዲሁም ወደ ፊት የፌዴሬሽኑ ጅምር ፕሮጀክቶች ሲደርሱ ግን ወደ ትክክለኛ መንገድ መግባት እንደሚቻል ተናግረዋል። በመጨረሻም ዋና ዓላማው ተተኪዎች ላይ ከመስራት አንፃር ቢሆንም በእሁዱ ጨዋታ ግን አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የሚችሉትን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።