የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 15ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ሀምበሪቾ ዱራሜ ከመመራት ተነስቶ ወሳኝ ድል ሲያስመዘግብ ጉለሌ እና ፌዴራል ፓሊስ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መሻሻሎችን ያሳየው ሀምበሪቾ ዱራሜ እና የካ ከፍለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ 8፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ መሪነት ተካሂዶ በሀምበሪቾ 3-2 አሸናፊነት ተገባዷል። 

ጨዋታውን በሚገባ በመቆጣጠር በተጋጣሚያቸው ላይ ገና በጊዜ ጫናዎች በማሳደር ብልጫ ለመውሰድ የጣሩት ሀምበሪቾዎች በተለይ ወደ ጎን የሜዳውን ክፍል በመለጠጥ በቅብብል ሂደት ጥቃት ለመሰንዘር ጥረቶችን አድርገዋል፡፡በተለይ በቀኝ መስመር በተሰለፈው አላዛር አድማሱ አማካኝነት ገና በጊዜ ወደ የካ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ቀኝ መስመር ባደላ ቦታ አላዛር አድማሱ ወደ ሳጥን የግል አቅሙን ተጠቅሞ አሻግሮ ልዑልሰገድ አስፋው አክርሮ ሲመታ በተከላካዮች ተደርቦ የወጣ ሲሆን ከሁለት ደቂቃ በኋላ በድጋሚ ልዑልሰገድ ከሳጥን ውጪ መትቶ በሚያስቆጭ መልኩ ወጥቶበታል፡፡

ለሀያ ደቂቃዎች ያክል ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት የካዎች በሂደት በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ዕቅድ በመጀመሪያ ሙከራቸው ጎል አስቆጥረው መሪ ሆነዋል፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል የተገኘ ረጅሙ ኳስ የሀምበሪቾ ተከላካዮች መዘንጋት ታክሎበት ካሳሁን ሰቦቃ ሳይቸገር ወደ ጎልነት ለውጦ የአሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው ቡድን ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወደ መነቃቃቱ የተመለሱት ሀምበሪቾዎች በተደጋጋሚ ግብ ለማግኘት ቢጥሩም አጋማሹ 1-0 ተገባዷል፡፡

ሁለተኛው አርባ አምስት ሲጀመር የመጀመሪያዎቹን አምስት ደቂቃዎች ሀምበሪቾ ዱራሜዎች መረጋጋት ተስኗቸው መልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ በነበሩት የካ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ግድ ብሏቸዋል፡፡ በ48ኛው ደቂቃ ፈጣን እንቅስቃሴን የተጠቀሙት የካዎች ካሳሁን ሰቦቃ በቀኝ በኩል ያገኘውን ኳስ ወደ ጎልነት በመቀየር ለራሱ እና ለቡድኑ የግብ መጠኑን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ሁለት ጎሎች ከመረባቸው ያረፈባቸው የአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ተጫዋቾች ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጣ ከፍተኛ የሆነ የጨዋታ ብልጫን ተጠቅሞ በቶሎ ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል።

በዚህም 52ኛ ደቂቃ ላይ ፈጣኑ ተጫዋች አላዛር አድማሱ ላይ የየካ ተከላካዮች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ልዑልሰገድ አስፋው ወደ ጎልነት ለውጧት ጨዋታው 2ለ1 ሆኗል፡፡ ያለ መታከት ሜዳ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በማሰብ ሀምበሪቾዎች ኪዳኔ አሰፋ እና ሰይፈ ዛኪርን ለውጠው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ ተጨማሪ ግብ አግኝተዋል፡፡ 55ኛ ደቂቃ በግራ የየካ የግብ ክልል ወደ መስመር ካደላ ቦታ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት የቀድሞው የደደቢት ተጫዋች ዳግማዊ አባይ ሲያሻማ የቡድኑ አምበል እንዳለ ዮሐንስ ቁመቱን ተጠቅሞ በግንባር በማስቆጠር ሲመራ የነበረውን ቡድን ወደ አቻነት አሸጋግሯል፡፡

ይበልጥ በሁለተኛው አጋማሽ ምቹነት የተሰማቸው ይመስሉ የነበሩት ሀምበሪቾዎች በሰይፈ ዛኪር፣ ኪዳኔ አሰፋ እና አላዛር አድማሱ አማካኝነት ወደ መሪነት የሚሸጋገሩበትን አጋጣሚዎች አግኝተው ሊጠቀሙ አልቻሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተቀይሮ የገባው አማካዩ ኪዳኔ አሰፋ መሀል ለመሀል በተከላካዮች ያሾለከለትን ኳስ ሁለት ጊዜ ወደ ሳጥን ገፋ ያደረገው አማካዩ ልዑልሰገድ አስፋው ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛዋን ጎል ከመረብ አዋህዷል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስምንት ያህል ቀሪ ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ወደ መመራት የተሸጋገሩት የካዎች ብልጫን በመውሰድ ተደጋጋሚ ዕድልን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይ አላዛር ዝናቡ ከርቀት መቶ የወጣበት እና ኤፍሬም ጌታቸው ቋሚ የመለሰበት ምንአልባት የካን ነጥብ ሊያጋሩ የቀረቡ ቢመስሉም ጨዋታው በሀምበሪቾ 3ለ2 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

10፡00 ላይ የተደረገው የአስራ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር የመዲናይቱ ሁለት ክለቦች ጉለሌ ክፍለ ከተማ እና ፌዴራል ፖሊስን አገናኝቶ አንድ አቻ ተጠናቋል። 

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስን መሠረት ባደረገ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ሚዛኑን የደፋ እንቅስቃሴን ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ጉለሌዎች ጥሩ ነበሩ። በአንፃሩ የአሰልጣኝ ተስፋዬ ፈጠነው ፌድራል ፖሊስ ተሻጋሪ ኳስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ይምሰል እንጂ አልፎ አልፎ ወደ ቀኝ መስመር በማድላት በአንተነህ ተሻገር አማካኝነት ግብ ፍለጋ ላይ ተጠምደው ነበር። በጨዋታው ከኳስ ጋር ተግባቦታቸው ከፍ ያለው ጉለሌዎች በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ የመጀመሪያ ሙከራን አድርገዋል፡፡

ዳዊት ሽፈራው ከቀኝ በኩል የተገኘን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ በቋሚ ብረቱ ታኮ የወጣበት ቀዳሚ ነበረች፡፡ ኃይል የተቀላቀለበትን ጨዋታ በመከተል እና ረጃጅም ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመላክ ለመጫወት ጥረት ያደርጉ የነበሩት ፌደራል ፖሊሶች 21ኛው ደቂቃ ላይ በራሳቸው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተከላካዩ በረከት በቀለ በሊዮናርዶ በቀለ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሥዩም ደስታ ወደ ጎልነት በመለወጥ ጉለሌን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ግብ ካስተናገዱ በኋላ በተሻለ መንቀሳቀስ የጀመሩት ፌዴራል ፖሊሶች በቻላቸው ቤዛ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ወደ ግብነት መለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በሁለተኛው አርባ አምስት ሙሉ በሙሉ ቢጫ ለባሾቹ ፌዴራል ፖሊሶች ያደርጉ የነበረው እንቅስቃሴ ሳቢ እና ለዕይታ ማራኪ ሆኖ የታየ ሲሆን በአንፃሩ ጉለሌዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው ብልጫ በተወሰነ መልኩ ቀዝቅዘው ታይቷል፡፡ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የጉለሌው ዳዊት ሽፈራው በሁለተኛው አጋማሽ 48ኛ ደቂቃ ላይ ግልፅ የሆነ አጋጣሚን አግኝቶ በሚያስቆጭ ቅፅበት አምክኖታል፡፡ ነገር ግን በሂደት የተሻለ አቀራረብን ሲያሳዩ የነበሩት ፌዴራል ፖሊሶች 77ኛው ደቂቃ ላይ ወደ አቻነት ተሸጋግረዋል፡፡ ታምራት እያሱ ላይ የጉለሌ ተከላካዮች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ኪሩቤል ዮሴፍ ወደ ጎልነት ለውጧት ቡድኑን 1-1 አድርጓል፡፡

ፋታ የለሽ የሜዳ ላይ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን የተከተሉት ፌዴራል ፖሊሶች በተደጋጋሚ ያለቀላቸውን ዕድሎች እያገኙ ሲያመክኑ ውለዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ የጉለሌው አማካይ ኦካይ ሉል ቢኒያም ካሳሁን ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ያጋሩ