የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የ15ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በምድብ ለ ተጠባቂ ሁለት ጨዋታዎች ስልጤ ወራቤ በሰፊ ጎል ሲያሸንፍ የለገጣፎ እና የቤንችማጂ ቡና ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ የነበረው ቡራዩ ከተማ እና ስልጤ ወራቤን አገናኝቶ ወራቤዎች ከጨዋታ ብልጫ ጋር 5-3 አሸናፊ ሆነዋል። የመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄን በመምረጥ እምብዛም ወደ ጎል አይደረሱ እንጂ ስልጤ ወራቤዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ክፍት ሜዳ ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ስልጤ ወራቤዎች በቀኝ መስመር ሙሀጅር መኪ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ራሱ ሙሀጅር አሻምቶት ሳዲቅ ሴቾ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል በ13ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል። ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ያልተቸገረው ስልጤ ወራቤ በ18ኛው ደቂቃ በቅብብሎሽ ተመስርቶ የመጣው ኳስ አምረላ ደልታ በጥሩ መንገድ ያሳለፈለትን በድሩ ኑርሁሴን በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት መቀየር ችሏል።

ዘግየት ብለው ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት ቡራዩዎች ከማዕዘን የተጣለውን ኳስ የመሐል ተከላካዩ በኃይሉ በግንባሩ ግጭቶት የወራቤ ተከላካዮች ያወጡበት ጥሩ ሙከራ ነበር። በዚህች ሙከራ የተነቃቁት ቡራዮዎች ከውሃ እረፍት መልስ በ35ኛው ደቂቃ በአማካዩ መለሰ ማሺሞ አማካኝነት የመጀመርያ ጎል አስቆጥረዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡራዩ ከተማዎች አከራካሪ ጎል አስቆጥረዋል። በ50ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲተፋው በቅርብ የነበረው ተከላካዮ በኃይሉ መሐመድ አግኝቶ ለቡድኑ አቻ የምታደርግ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ስልጤ ወራቤዎችም ጎሉ የተቆጠረው የግብ ጠባቂያችን ስንታየሁ ኳሱን እንዳይዝ ሚዛኑን ካሳተው በኃላ ነው በማለት ቅሬታ አቅርበዋል። ከዚህ የአቻነት ጎል በኋላ ጨዋታው ውጥረት የተሞላበት ሆኖ ቀጥሎ ስልጤ ወራቤዎች ዳግመኛ መሪ መሆን የቻሉበትን ጎል አግኝተዋል። የመስመር አጥቂው አምረላ ደልታታ የማዕዘን ምት መምቻው ጋር የነጠቀውን ኳስ ወደ ጎል ሲያሻግረው የቡራዩው ተከላካይ በኃይሉ መሐመድን ጨርፋ በራሱ ላይ 61ኛው ደቂቃ በማስቆጠር ወራቤዎች የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል።

በድጋሚ የአቻነት ጎል ፍለጋ ቡራዩዎች በሙሉ አቅማቸው ለማጥቃት ወደ ፊት በሚሄዱበት ወቅት የሚገኘውን ክፍት ሜዳ ደጋግመው በመጠቀም የቡራዩን መረብ የፈተሹት ስልጤዎች በ74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ገብቶ በጉዳት ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ከመስመር እየተነሳ ልዩነት ሲፈጥር የነበረው በረከት ወንድሙ ለቡድኑ አራተኛ ጎል ከመረብ አሳርፏል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል ከተሻጋሪ ኳስ ቡራዩዎች በ89ኛው ደቂቃ በአንበላቸው መለሰ ማሺሞ የግንባር ኳስ ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በተጨማሪ ደቂቃ በዕለቱ ጥሩ ዕለት ያሳለፈው ሙሀጂር መኪ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ማሳረጊያ አምስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

ሌላኛው የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብር ቤንችማጂ ቡና ከ ለገጣፎ ለገዳዲ ያገናኘው ጨዋታ በርከት ያሉ ውዝግቦችን አስተናግዶ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ገና ሳይጀምር ቤንችማጂ ቡናዎች የተጫዋች ተገቢነት ክስ አሲዘው በጀመረው ጨዋታ የጎል ዕድል በመፍጠር ቀዳሚ የሆኑት ለገጣፎዎች በአምስተኛው ደቂቃ በፋሲል አስማማው የግንባር ኳስ የግቡ አግዳሚ በመለሰባቸው ነበር። ጨዋታው በጥሩ ግለት ቢጀምርም የኋላ የኋላ ወደ መቀዝቀዝ አምርቶ 32ኛው ደቂቃ ጣፎዎች ጎል አግኝተዋል። ከቀኝ መስመር የተጣለውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ፋሲል አስማማው በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ ጎል አስገኝቷል።

ይህንን ጎል ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት ቤንችማጂ ቡናዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። ክርክሩ የተወሰነ ደቂቃ ከወሰደ በኋላ ጨዋታው እንዲጀምር እንደተደረገ በአስደናቂ ሁኔታ በቀጥታ ኳሱን ከመሐል ሜዳ በግራ እግሩ በመምታት ኤፍሬም ታምሩ የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። የዚህ ጎል መቆጠር ሂደት ተገቢ አይደለም ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል ኳሱን ወደ ውጭ አውጥቶታል በማለት ጨዋታው ወደ ሌላ ጭቅጭቅ አምርቷል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሀይል አጨዋወት በዝቶበት እንቅስቃሴው ሲቆራረጥ ታይቷል። ጨዋታውንም ለመቆጣጠር የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ አስራ አንድ ቢጫ ለሁለቱ ቡድኖች ከመስጠታቸው ባሻገር የለገጣፎው ታምራት አለማየሁ ቤንችማጂ በኩል ጌታሁን ገላዬ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል። ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።