አምስቱ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ዋልያውን አመሻሽ ላይ ተቀላቅለዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጠዋት በሰራነው ዘገባ ከኢትዮጵያ ቡና የተመረጡት አምስቱ ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድኑን እንዳልተቀላቀሉ አመላክተን የነበረ ሲሆን አሁን ከመሸ ተጫዋቾቹ ቡድኑን መቀላቀላቸውን አውቀናል።

መጋቢት 16 ከኮሞሮስ አቻው ጋር ከሜዳው ውጪ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል። ከኢትዮጵያ ቡና 5 ተጫዋቾች እና በግብፁ ክለብ አል-ጎውና ከሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ውጪ የሚገኙ ተጫዋቾችም ጁፒተር ሆቴል ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ ተሰባስበው የህክምና ምርመራ አድርገው ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ከመሸ በደረሳት መረጃ ደግሞ አምስቱ የቡና ተጫዋቾች ስብስቡን ተቀላቅለዋል።

በዚህም የግብ ዘቡ አቤል ማሞ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ዊልያም ሰለሞን ቀደም ብለው ብሔራዊ ቡድኑ የተቀላቀሉ ሲሆን አቡበከር ናስር እና አስራት ቱንጆ ደግሞ ከደቂቃዎች በፊት ጁፒተር ሆቴል ደርሰዋል።

በተያያዘ ዜና ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ከ10 ሰዓት ጀምሮ የመጀመሪያ ልምምዱን በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ሰርቷል። በልምምዱም የአካል ብቃት ምዘና እና ቀለል ያሉ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር አውቀናል። አምስቱ የቡና ተጫዋቾች ግን አምሽተው ስለደረሱ በመጀመሪያው የልምምድ መርሐ-ግብር አልተሳተፉም።