የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ከሜዳ ጋር በተያያዘ ሀሳባቸውን አጋርተዋል

👉”ሀገሪቱ ውስጥ ሁሉን ያሟላ ሜዳ የለም”

👉”የሲሚንቶ ቁልል ግን በየቦታው አለ”

ዛሬ በተደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተነሱ አዳዲስ ጉዳዮችን ከስር ከስር እየተከታተልን ያቀረብን ሲሆን የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከሜዳ ጋር ተያይዞ የተናገሩትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ኳስ ከጀመርን 80 ምናምን ዓመት አልፎናል። ግን እውነቱን ስናገር ሜዳ የሚባል ነገር የለንም። የሲሚንቶ ቁልል ግን በየቦታው አለ። አብዛኞቻችን ሀዋሳ ጥሩ ከተማ ናት፣ የመለማመጃ ሜዳም አላት ብለን ነበር። ግን ወደእዛ ሄደን ጨዋታ የምናስጀምርበት መጫወቻ ሜዳ አጥተን የዩኒቨርስቲውን ፕሬዝዳንት እኔው ራሴ ከሁለት ጊዜ በላይ ተመላልሼ ነው ያገኘነው። እሱም ሜዳ ቢሆን እኛ ከሄድን በኋላ ተስተካክሎ የተሰራ ነው። ሀዋሳ ውስጥ ሜዳ የለም ብንላችሁ ታምናላችሁ? በሀገር ደረጃ የተሰሩ ሜዳዎች አሉ። ተሰርተው ግን ያላለቁ። ሁላችንም ወደ ድሬዳዋ ስንሄድ የምናቀው የአሸዋ ሜዳ እንዳሉ ነበር። እናንተም የአሸዋ ሜዳ አንለማመድም አላችሁ። ድሬዳዋ የሌለውን አምጣ ማለት አንችልም።

“16 ቡድን አንድ ከተማ ላይ ሲቀመጥ በዛ ከተማ ከፍተኛ ጫና ነው የሚፈጠረው። አንዱም በመለማመጃ ሜዳ ጉዳይ ነው። ሀዋሳ ላይ አንድ ጥሩ ሜዳ አለ። ያንን ሜዳ ሲዳማ ብቻ ነው የሚለማመድበት ሌሎች አትለማመዱም ተብሎ ተከልክለው ነበር። ይህ ፍትሀዊ አይደለም። ለቦርድ አመራሮች ነግረን ብዙ ተጨቃጭቀን ነው የተፈቀደው።

“ይህ ብቻ ሳይሆን የልምምድ ሜዳዎቹ ላይም ከፍተኛ ሂሳብ እንዲከፈል ተጠይቆ ነበር። ወደ ከተማዎች ስንሄድ ሆቴሎች ሂሳባቸውን ይጨምራሉ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሉ። እኛ ግን ወደ ከተማው ስንሄድ ከከንቲባው ጋር ቁጭ ብለን መሰል ችግሮች እንደማይፈጠሩ ተወያይተን እና ተስማምተን ነው። በኋላ ግን የእናንተው (ክለቦች) ቡድን መሪዎች እና ሥራ-አስኪያጆች ናቸው እንዲጨመር ተስማምተው የምናገኛቸው። ስለዚህ መጀመሪያ ራሳችንን እንጠይቅ። ሜዳን በተመለከተ ግን ሀገሪቱ ውስጥ ሁሉን ያሟላ ሜዳ የለም።”

ያጋሩ