👉 “ማንም ሰው ከስምንተኛ ክፍል እና ከአምስተኛ ክፍል ወጥቻለው ብሎ ወደ ዳኝነት መግባት የለበትም”
👉 “ፕሪምየር ሊጉ ከሚያገኘው ገንዘብ ዳኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ክፍያቸውን አሳድገን ነበር…”
ከሰዓታት በፊት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስቸኳይ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የብዙዎች ሀሳብ የነበረው የዳኝነት ክፍተቶችን በተመለከተ የሊጉ የበላይ አካል የሆነው የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ሲያጋሩ ተደምጧል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ይህንን ብለዋል።
“ዳኝነቱ ባለፈው ዓመት ካየነው በዚህ ዓመት በባሰ ሁኔታ ችግሮች ተከስተውበታል። እነዚህን ችግሮች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር (ከፕሬዝዳንቱም ጋር ጭምር) ቁጭ ብለን ተወያይተንበታል። በዚህም መሠረት ጥፋት ያጠፉ ዳኞች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገናል። ይህ ቢሆንም እርምጃዎቹ ተወስደው ጥፋቶቹ ከመከሰት አልቆሙም። ለምን እንደሆነ አይገባኝም። ኢንተርናሽናል ዳኞችን ጨምሮ ማንኛውም ዳኛ ካጠፋ መቀጣት ይኖርበታል። ተወያይተን ፕሪምየር ሊጉን የሚመጥኑ ዳኞች እንዲመደቡልን ብናደርግም ችግሩ በድጋሜ ተከስቷል።
“ይህ ችግር በአንድ ምሽት አይወገድም። ፕሪምየር ሊጉ ከሚያገኘው ገንዘብ ዳኞች ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ክፍያቸውን አሳድገን ነበር። እኛ ይህንን ክፍያ የምንከፍለው ልምድ እና እውቀቱ ያላቸው ዳኞችን ለማበረታታት ነው። ከመቅፅበት ስለሆነ ውሳኔዎች የሚወሰኑት ስህተቶች ይሰራሉ። አንዳንዶቹ ግን ከመቅፅበት የተከሰቱ ችግሮች አይደሉም። በአንድ ወቅት ክፍያውን መጨመራችን ከሆነ ችግሮቹን ያባባሰው ክፍያውን እንቀንሰው ብለንም ውይይት አድርገናል። እንደምታውቁት የዳኝነት እና የፍትህ ጉዳዮች የፌዴሬሽኑ ናቸው። ግን በስልጠናዎች ለማስተካከል ይሞከራል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ እኛ ከአጋሮቻችን ጋር በመተባበር የምናዘጋጃቸው ይኖራሉ። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ በሚያዘጋጀው ስልጠና ወደ 600 ሺ ብር እኛ እንጨምራለን ብለናል። በዓመቱ መጨረሻ አካባቢም በሱፐር ስፖርት የሚሰጥ ስልጠና ይካሄዳል። ስለዚህ ይህንን እናሻሽላለን። የምናሻሽለው በስልጠና ነው።
“ከዚህ ውጪ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከመጀመሪያው ዳኞችን ሲመለምል የራሱን መመዘኛዎች ማሻሻል ያለበት ይመስለናል። ማንም ሰው ከስምንተኛ ክፍል እና ከአምስተኛ ክፍል ወጥቻለው ብሎ ወደ ዳኝነት መግባት የለበትም። ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት መስፈርት መሟላት አለበት። ከዚህም በመቀጠል በታችኛው ሊግ ላይ የሚያሳየውም ብቃት እና ልምድ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።”
አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች ያነሱት ይህ የዳኝነት ህፀፅ ላይ ሀሳቦች ከተንሸራሸሩ በኋላ በስፍራው የተገኙት እና ዳኞችን ከሚመድበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጡት ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አበበ ገላጋይ እና ዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ክፍተቱን ለማረም በቀጣይ የጋራ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።