ከፍተኛ ሊግ | ከአስደናቂ ግስጋሴው በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የተቀዛቀዘው ነጌሌ አርሲ አጨራረሱን ያሳምር ይሆን ?

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች እድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍም ነጌሌ አርሲን እንመለከታለን።

[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]

ደረጃ፡ በ28 ነጥቦች 2ኛ (ከመሪው ኤሌክትሪክ በአራት ነጥቦች ርቋል)

የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች

16ኛ ሳምንት፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
17ኛ ሳምንት፡ ከጋሞ ጨንቻ
18ኛ ሳምንት፡ ከገላን ከተማ

ከፍተኛ ሊጉ በአዲስ አወቃቀር በ2008 ሲጀመር ከነበሩ ቡድኖች አንዱ የነበረው ነጌሌ አርሲ በ2009 ወደ አንደኛ ሊግ ቢወርድም መልሶ በማገገም 2011 ላይ በድጋሚ የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎን ማሳካት ችሏል። ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ የተፎካካሪነት ታሪክ የሌለው ከመሆኑ በተጨማሪ ዓምና በምድብ ሐ ተደልድሎ ባደረገው ውድድር ያጋጠመው የመኪና አደጋን ጨምሮ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ የውድድር ዘመኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀለው አርባ ምንጭ ከተማ በ25 ነጥቦች በማነስ 6ኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው።

ቡድኑ ለ2014 የውድድር ዘመን ባደረገው ቅድመ ዝግጅት ከ16 በላይ ተጫዋቾችን ከማስፈረሙ በተጨማሪ ዐምና የመሩት አሰልጣኝ ታዬ ናኒቻን በቀድሞ አሰልጣኙ ራሕመቶ መሐመድ በመተካት የውድድር ዓመቱን ጀምሯል።

”ሰጎኖቹ” ከዚህ ቀደም ከነበራቸው የተሳትፎ ታሪክ ፣ ከዐምና ውጤት እና በቅድመ ውድድር ከነበረው መጠነ ሰፊ የስብስብ እና አሰልጣኝ ለውጥ አንፃር በዚህ ደረጃ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ የሚል ግምት ያሳደሩ የስፖርት ቤተሰቦች እምብዛም ነበሩ። ሆኖም የተገላቢጦሽ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር በተለይ እስከ 15ኛው ሳምንት ድረስ አንገት ለአንገት ተናንቀው መዝለቅ ችለዋል። የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ራህመቶ መሐመድም ቡድኑ ከተፎካካሪዎቹ አንፃር በአነስተኛ በጀት ምርጥ ጉዞ በማድረግ እዚህ ደረጃ የመድረሱን ምስጢር አንዲህ ሲል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል። “አምና እኔ የነበርኩት በአንደኛ ሊግ በነበረው ሞጆ ከተማ ነበር። ወደዚህም ስመጣ አብዛኛዎቹን ልጆች ከአንደኛ ሊግ ነበር ይዤ የመጣሁት እንግዲህ ከክለቦች አንስቶ እኛ አሰልጣኞችን ጨምሮ ስም እና በሊጉ አውድ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የማመን ዝንባሌ አለ። ይህም በእግር ኳሳችን ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። ይህ በወጣት ተጫዋቾች ያለማመን ጉዳይ ነው እንጂ አሁን እኔ ጋር ያሉት አብዛኞቹ ልጆች ከአንደኛ ሊግ (ቢሾፍቱ ከተማ ፣ ሞጆ ከተማ ፣ ሐረር ከተማ ፣ ቡሌ ሆራ ) የመጡ ተጫዋቾች ናቸው። በክለቦች ብቻ ሳይሆን በእኛ አሰልጣኞች ዘንድ ቡድን ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ ካልተመደበልን የሚሆን አይደለም ብለን እናምናለን። እንጂ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት ከተቻለ የእኛም ሆነ ሌሎች ጥቂት ቡድኖች ምሳሌ መሆን እየቻሉ ነው።” ብለዋል።

አምቦ ከተማን 1-0 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ነጌሌ አርሲዎች በሁለተኛው ሳምንት በኤሌክትሪክ ከተሸነፉ በኋላ እስከ 10ኛው ሳምንት ድረስ ሽንፈት የሚባል ነገር አላዩም ነበር። በዚህም ምድቡን ለመምራት እስከመብቃት ደርሰው ነበር፤ በ11ኛው ሳምንት በኤሌክትሪክ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ሽንፈት አስተናግደው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተመለሱ እንጂ። ሆኖም ብዙሃኑ የቀድሞዎቹ ታላላቅ ክለቦች ኤሌክትሪክ እና ባንክ ላይ ዓይኑን ሲጥል እነርሱ ግን ድንቅ ጉዞ በማድረግ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ በሁለቱ መሐል ተገኝተው ብዙዎችን አስደንቀዋል። ” እስከ አሁን በውድድሩ የነበረን ጉዞ ከሞላ ጎደል በጣም ጥሩ የሚባል ነበር። ስህተቶችን እያረምን ጠንካራ ጎኖችን እያጎለበትን እዚህ ደርሰናል። እስከ ሀላባ ከተማው ጨዋታ (13ኛ ሳምንት) ድረስ የነበረን ነገር በጣም ጥሩ የሚባል ነበር። እንደ ቡድን ለፍተናል ልጆቹም የሚባሉትን የሚሰሙ ሜዳ ላይ ከራስ ጥቅም ይልቅ ለቡድን ውጤት የሚታትሩ ነበሩ። በዚህም ጥሩ ውጤት ማምጣት ችለናል።” በማለት አሰልጣኝ ራህመቶ የቡድናቸውን ጉዞ ገልፀውታል።

የቡድኑ የአንደኛ ዙር ምርጥ ጉዞ ከፍተኛ ጫና እና የብዙሃን ትኩረት በሚያይልበት ሁለተኛ ዙር መደገም አልቻለም። በአንደኛው ዙር ከሰበሰበው 20 ነጥብ ላይ ያከለውም ስምንት ነጥቦች ብቻ ነው። ይህም ማለት ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች መሰብሰብ ከነበረበት 18 ነጥብ አስሩን ጥሏል ማለት ነው። አሰልጣኝ ራህመቶ እንዳሉትም ከሀላባው ጨዋታ ወዲህ ነጌሌዎች በነበሩበት ፍጥነት መጓዝ አልቻሉም። ” ባለፉት ጨዋታዎች የነበረን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እኛን የማይወክል እና ቅርፅ አልባ ነበር። እንደ ቡድን ይንቀሳቀስ የነበረው ቡድናችን በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ግን ግለሰባዊነት አይሎበት ተመልክተናል። ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የነበሩ ጫናዎች የቡድኑን ሂደት አበላሽተውብናል። በተለይም ጌዲዮ ዲላን እና ባቱን የገጠመው ቡድን አርሲ ነገሌ ነው ብሎ ለመናገር እስኪያስቸግር ድረስ ደካሞች ነበርን።”

ነጌሌ አርሲ በብዙ መመዘኛዎች እስካሁን ያሳካው ስኬት በራሱ ከፍ ያለ ውዳሴ የሚያስቸረው ቢሆንም በቅርብ ጨዋታዎች ያሳየውን መዳከም መንስኤ ጠቁሞ ማለፉ አስፈላጊ ይሆናል። እንደ አሰልጣኝ ራህመቶ እምነትም እንደ ቡድን የመጫወት ድክመታቸው በተጨማሪ ሌሎች ዋንኛ ምክንያቶች ይነሳሉ

“በዋነኝነት ቡድኑ ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ ከነገሌ ከተንቀሳቀስን ጀምሮ አንድም አካል ቡድኑን ለማነጋገርም ሆነ ለማበረታታት የመጣ አካል የለም። የትኛውም አካል ለሰራው ሥራ እውቅና መስጠት ተገቢ ነው። እኛ ጋር ግን አንድም አካል ይህን ሲያደርግ አልተመለከትንም ፤ ይሄም ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ሁለተኛው ጉዳይ በተጫዋቾቻችን ዘንድ ያለው ከፍተኛ ጉጉት በራሱ ችግር ፈጥሮብናል። የቤት ሥራችን በአግባቡ ተወጥተን ሳንጨርስ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መቃረባችን ተከትሎ በተወሰነ መልኩ ተጫዋቾቻችን ላይ ጫና አሳድሮብናል። በዚህም ጨዋታዎችን ሳናደርግ ወደ ሜዳ ከመግባታችን በፊት አሸንፈናል የሚለው እሳቤ ችግር ፈጥሯል። በተጨማሪም ከተቃራኒ ቡድኖች የሚመጡ ጫናዎች እንዲሁም በተለይም በመጀመሪያው ዙር ከዳኞች ከውድድር እና ሥነስርአት ይመጡ የነበሩ ጫናዎች ከልጆቻችን ጥሩ አለመሆን ጋር ተዳምሮ ውጤታችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሮብናል። እነዚህ ሁኔታዎች በቡድናችን ከ85% የሚልቁት ተጫዋቾች ልምድ አልባ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በመሰል ጫና ውስጥ ለመጫወት ሊቸገሩ ይችላሉ። ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች በጀመርንበት መንገድ በውድድሩ ለመዝለቅ ተቸግረናል ብዬ አስባለሁ።”

የነጌሌ አርሲ የውድድር ዘመን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ሦስት ጨዋታዎች ከፊቱ ይገኛሉ። በእርግጥ ጨዋታዎቹ ብቻ ሳይሆን የተፎካካሪዎቸ ነጥብ መጣልም እኩል ድርሻ ይኖረዋል። ለጊዜው በነጥብ ከሚስተካከላቸውና በሁለተኛው ዙር አስገራሚ መሻሻል ካሳየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሰኞ በ4፡00 የሚያደርጉት ጠንካራ ፍልሚያ የጉዟቸው መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ጨዋታ ነው። ካሸነፉ አንደኛውን ተፎካካሪ (ባንክ) ወደ ኋላ አስቀርተው ኤሌክትሪክ ላይ ጫና ማሳደር ይችላሉ። ሽንፈት ወይም የአቻ ውጤት ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ውጥናቸውን የማስተጓጎል አቅም ይኖረዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው ባንክን የሚገጥሙት አሰልጣኝ ራህመቶ “እውነት ለመናገር በሁለተኛው ዙር ንግድ ባንክ በብዙ መንገዶች ተሻሽሎ ቀርቧል። በእኛ ዘንድ ግን የነበረውን ነገር ነው ይዘን የቀጠልነው። ስለዚህ እንደቡድን ባለን ነገር ተጠቅመን ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘን ለመውጣት ከፈጣሪ ጋር ዝግጅታችንን አጠናቀናል።” ሲሉ ያደረገትን ዝግጅት በአጭሩ ገልፀዋል።

ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚገቡ ቡድኖችን የሚያሳውቁ የመጨረሻ ምዕራፍ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች በተቃረቡ ቁጥር በተሳታፊ ክለቦች ዘንድ አንድ ስጋት ተደርጎ የሚወሰደው የዳኝነት ሁኔታ ነው። ይህን ተከትሎም በተለይ የፕሪምየር ሊጉ እረፍት ላይ መሆንን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሊጉ ሲዳኙ የምናውቃቸው ዳኞች የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎችን እንዲመሩ መደረጉ በችግሩ ዙርያ ያለውን ስጋት መጠኑ የቀረፈው ይመስላል። ከፊቱ ሦስት ወሳኝ ጨዋታዎች የሚጠብቁት አርሲ ነገሌም ግን ይህ ጉዳይ እንደማያሳስበው አሰልጣኝ ራህመቶ የውድድሩን የእስካሁኑ አመጣጥ ላይ በመንተራስ ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል። “በተለይም በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች የተመለከትነው ዳኝነት እኔ በግሌ እንከን የለሽ ነበር። በቀጣይ ያለውን ሂደት አሁን ላይ ሆኜ መናገር ባልችልም ፌደሬሽኑ ግን በመጀመሪያው ዙር የነበሩ የዳኝነት ክፍተቶችን ለማረም የሄደበት ርቀት የሚደነቅ ነው። ከዚህ መነሻነት ባለማወቅ ከሚሰሩ ውስን ስህተቶች ውጪ ሆን ተብለው የሚሰሩ ስህተቶችን አንመለከትም በዚህም ፍትሃዊነት ዳኝነትን እየተመለከትን እንገኛለን ብዬ አስባለሁ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሆነ የዳኞች ኮሚቴ ለውድድሩ ጥሩ ትኩረት ሰጥተው እያደረጉት የሚገኘውን ጥረት በዚሁ አጋጣሚ ለማድነቅ እና ለማመስገን እፈልጋለሁ።” ሲል ሀሳቡን አጋርቶናል።

ቡድናቸው ከኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የአራት ነጥብ ልዩነት አጥብቦ የማለፍ ዕድሉን እስከመጨረሻው አሟጦ ለመጠቀም ባለፉት ቀናት ተደጋጋሚ ውይይቶችን ከተጫዋቾቹ ጋር ማድረጋቸውን የገለፁት አሰልጣኝ ራህመቶ ” ከእኛ የሚጠበቀውን ማለትም የቀሩትን ጨዋታዎች በድል ለመወጣት ተነጋግረናል። የእነሱ መሸነፍ እና ማሸነፍ ሌላ ጉዳይ ነው። ስለዚህ የተነጋገርነው ራሳችንን በተሻለ ቦታ ለማግኘት በእጃችን ያለውን ዘጠኝ ነጥብ አሳክተን የሚሆነውን ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል።” ሲሉ ቀጣይ እቅዳቸውን ገልፀዋል።

ወደ ፕሪምየር ሊግ የማለፍ እድሉ በኤሌክትሪክ ውጤት ላይ የተመሰረተው ነጌሌ አርሲ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ መግቢያውን በር ይከፍት ይሆን ?