ስድስት ተጫዋቾች ከዋልያዎቹ ስብስብ ተቀንሰዋል

ከኮሞሮስ ጋር ለሚደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስድስት ተጫዋቾችን መቀነሱ ታውቋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ መከናወኛ ወቅት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከኮሞሮስ አቻው ጋር ከሜዳው ውጪ ለማድረግ መጋቢት 16 ቀጠሮ እንደያዘ ይታወቃል። ለዚህ ጨዋታ ይረዳ ዘንድም የቡድኑ አሠልጣኞች ለ30 ተጫዋቾች ባለንበት ሳምንት አጋማሽ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ትናንት እና ከትናንት በስትያም ልምምዳቸውን አከናውነዋል።

ዛሬ ረፋድ ቡድኑ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምዱን ሲያከናውን ሶከር ኢትዮጵያ በቦታው ተገኝታ እንደተመለከተችው ደግሞ ስድስት ተጫዋቾች ከቡድኑ ተቀንሰዋል። ከአዲስ አበባ ከተማ የተመረጡት ዳንኤል ተሾመ እና ፍፁም ጥላሁን ፣ የፋሲል ከነማው ዓለምብርሃን ይግዛው ፣ የወልቂጤው አብዱልከሪም ወርቁ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ በረከት ወልዴ እና የኢትዮጵያ ቡናው ዊልያም ሰለሞን ከስብስቡ የተቀነሱ ሲሆን ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ተጫዋቾች ለኮሞሮሱ ጨዋታ አሰልጣኝ ውበቱ የሚጠቀሙባቸው ተጫዋቾች መሆናቸው ታውቋል።

ግብ ጠባቂዎች

ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ አቤል ማሞ

ተከላካዮች

አስራት ቱንጆ ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ አስቻለው ታመነ ፣ ያሬድ ባየህ ፣ ምኞት ደበበ ፣ መናፍ ዐወል

አማካዮች

አማኑኤል ዮሐንስ ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ሽመልስ በቀለ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ይሁን እንዳሻው ፣ ቢኒያም በላይ

አጥቂዎች

በረከት ደስታ ፣ አቡበከር ናስር ፣ ይገዙ ቦጋለ ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ፣ ዳዋ ሁቴሳ ፣ መስፍን ታፈሰ