ከፍተኛ ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምልሰቱን በድል ያጅባል ?

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የቀሩት የ3 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። ከየምድቡ አንድ ቡድን ብቻ በሚያልፍበት በዚህ ውድድር ላይ ከሦስቱ ምድቦች ዕድሉ ያላቸው ስምንት ቡድኖች ቀጣይ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞ እና ቀጣይ ተስፋዎችን በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል። በዚህ ፅሁፍ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንመለከታለን።

[የፅሁፍ ቅደም ተከተሉ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚያደርጉበት ወቅትን ታሳቢ ያደረገ ነው]

ደረጃ፡ በ28 ነጥቦች 3ኛ (ከመሪው ኤሌክትሪክ በአራት ነጥቦች ርቋል)

የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች

16ኛ ሳምንት፡ ከነገሌ አርሲ
17ኛ ሳምንት፡ ከገላን ከተማ
18ኛ ሳምንት፡ ከአምቦ ከተማ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ የወንዶች ቡድን ታሪክ 2009 ላይ ቆሞ ቆይቶ ዘንድሮ በድንገት ወደ እግርኳሳችን ካርታ ተመልሷል። ዓመታትን የተለያዩ እርከኖች በማሳለፍ ወደ ላይ ከፍ ከማለት ይልቅ በከፍተኛ ሊጉ ተወዳዳሪ የነበረው ኢኮሥኮን በመረከብ የስም ለውጥ ማድረግን ምርጫው ያደረገው ንግድ ባንክ ከጊዜ ጋር ተሽቀዳድሞ ነገሮችን በፍጥነት በመከወን ነበር የ2014 የውድድር ዘመንን የጀመረው።

ባንክ ኢኮሥኮን ይረከብ እንጂ በስብስቡ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ለውጥ በማደረግ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛውን የክለቡ አሰልጣኝ እንዲሁም ክለቡን የሚያውቁት ሲሳይ ከበደን በምክትልነት በመቅጠር አዲስ መልክን ይዞ ነበር የቀረበው። በእርግጥ አሰልጣኙም ሆነ ተጫዋቾቹ ለሊጉ አዲስ ባይሆኑም በፍጥነት ነገሮችን መልክ አስይዞ ለመፎካከር ጊዜ መውሰዱ አይቀሬ ከመሆኑ አንፃር የባንክ ጉዞ ጥሩ የሚባል ነው። ቡድናቸው ስለመጣበት መንገድ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛውም ይህን ነጥብ የሚያጠናክር ሀሳብ አጋርተውናል። ” እንደ ቡድን እኛ በዚህ ሊግ የመጀመሪያችን ነው። ቡድናችንም ዘግየት ብሎ ነው የተዋቀረው። ሌሎች ቡድኖች ወደ ዝግጅት ገብተው በመጨረሻ ሰዓት ነው ተጫዋቾች አሰባስበን ወደ ውድድር የገባነው። የውድድር ዓመቱን ዘግየት ብለን ብንጀምርም ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ወደ ቡድናችን ቀላቅለን ከወጣቶች ጋር ያወቀርን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከዚህም በተሻለ ርቀት እንጓዛለን የሚል ተስፋ ይዘን ነው ወደ ውድድር የገባነው። በውድድሩ ላይም ያየነው እንቅስቃሴ ይህንኑ ነው። ከውጫዊ ድክመቶች ውጪ በራሳችን ድክመት ያጣናቸው ውጤቶች አሉ። ነገር ግን እንደውድድር የተሻለ የሚታይ ቡድን ገንብተን ስለሆነ የቀረብነው እየሄድንበት ያለውም መንገድ ተስፋ ሰጪ ነው። እንደ ቡድን ጥሩ ቡድን ነው ብዬ መናገር እችላለሁ። ከዚህ አንፃር ስናየው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን ለመቅረብ የምንችለውን አድርገናል። አሁንም ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ተስፋው እጃችን ላይ ነው። በዚህም ደረጃ እስካሁን የመጣንበትም መንገድ ጥሩ ነው። ዳኝነትን በተመለከተ ግን ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በውድድሩ ላይ ከአንድም ሦስት አራት ጊዜ ዳኞች የተቀየሩበት ከዛም አልፎ ውድድሩን የሚመራው አካልም የተቀየረበት የፌዴሬሽን ሰዎችም ሁለት ሦስቴ እዚህ ምድብ ላይ በመገኘት የተነጋገሩበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ ክለቦች አሉ ፤ የተጎዱም ክለቦች አሉ።”

ከምድቡ መሪ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርቶ ውድድሩን የጀመረው ባንክ በቀጣይ አምስት ጨዋታዎችም ሽንፈት ባያስተናግድም ከስድስት ሳምንት አራቱን አቻ ተለያይቶ መጥፎ የማይባል ጅምር ማድረግ ችሏል። ሆኖም በቀጣይ በነጌሌ አርሲ እና ገላን ከተማ የደረሱበት ተከታታይ ሽነፈቶች ከምድቡ አናት እያራቀው መጥቶ ነበር። የአንደኛውን ዙር አምቦ ከተማን አሸንፎ ቢያጠናቅቅም ከመሪው ኤሌክትሪክ በስምንት ነጥቦች ርቆ መቀመጡ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገውን ጉዞ እንቅፋት የበዛበት አስመስሎታል።

ሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ የተለየው ባንክን ያስመለከተ ነበር። መሪው ኤሌክትሪክን 2-1 በማሸነፍ ዙሩን የጀመሩት ሀምራዊዎቹ ካደረጓቸው 6 ጨዋታዎች አምስቱን በማሸነፍ በሁለተኛው ዙር ከየትኛውም የምድቡ ተሳታፊ የበለጠ ነጥብ ማግኘት ችለዋል። ከኤሌክትሪክ ጋር የነበራቸውን ልዩነትም ወደ አራት ማጥበብ ችለዋል። የዚህ ከፍተኛ መሻሻል ምስጢር በሒደት የመሻሻል ውጤት ስለመሆኑም አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ይናገራሉ።

” ዘግይተን እንደመጀመራችን ቡድኑ እየተገነባ የሄደው በውድድር ላይ ነው። በእያንዳንዱ ጨዋታ ክፍተቶቻችንን እያረምን በቀጣይ ጨዋታ በተገቢው ሁኔታ እየተዘጋጀን የሄድንበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ ደግሞ የሚያሳየው ቀድም ብሎ የተደራጀ ቢሆን እና በክፍተቶች ላይ እየሞላን እያጠናከርን ብንመጣ ይሻል እንደነበር ነው። እኛ ባለንበት ምድብ ውስጥ አምቦ ነው ከአንደኛ ሊግ የመጣው ቡድን ፤ ከዛ ውጪ እኛ ነን ለውድድሩ አዲስ የሆንነው። ሌሎቹ ስምንቱ ግን በሊጉ የቆዩ ናቸው። አምቦም ቢሆን ከታች ሲመጣ የገነባውን ቡድን እያሳደገ ነው ውድድሩን የቀጠለው። እንግዲህ በአንፃራዊነት ሲታይ የእኛ ቡድን ነው እንደ አዲስ 25 ተጫዋች ይዞ ውድድሩን የተቀላቀለው። በእግርኳስ ባህሪ ደግሞ ቡድን በአንድ ጀንበር የሚገነባ አይደለም። ቡድን በደንብ እየተገነባ እየተብላላ የሚሄድ በመሆኑ እና እኛ እንደ አዲስ በመጀመራችን እንዲሁም ክለቡ ፈርሶ የነበረ በመሆኑ ግብዓት የሚሆን ቡድን ስላልነበረን በውድድር ውስጥ ነው ቡድን እየገነባን ያለነው። ከአንደኛው ዙር ሁለተኛው ዙር የተሻለ ውጤት ያስመዘገብንበት ትልቁ ምክንያት ይህ ነው ብዬ ነው የማስበው።”

እርግጥም ቡድኑ ያሳየው መሻሻልን የከፍተኛ ሊጉ የጨዋታ ቁጥር ውስንነት ገደበው እንጂ የጨዋታ ሳምንታት በገፉ ቁጥር ይበልጥ መሪው ላይ ጫና እያሳደረ የመሄድ ዕድልን ባገኘ ነበር። አንድ ቡድን 18 ጨዋታ ብቻ በሚያደረግበት ሊግ ላይ በአንድ ጨዋታ የሚጣል ነጥብ ብቻውን ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው። አሰልጣኝ ደግአረገም የጨዋታዎች ብዛት ለቡድናቸው ይሰጠው ከነበረው ጥቅም አንፃር ብቻ ሳይሆን ለፕሪምየር ሊግ ከመዘጋጀት አንፃርም ይመለከቱታል።

“በውድድሩ ፎርማት ውስጥ የጨዋታዎች ቁጥር ማነሳቸው የራሱ ክፍተት አለው። ምክንያቱም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት የሚወዳደሩ ቡድኖች በብዙ ጨዋታዎች ተፈትነው ቢሆን ላይም ሲሄዱ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀርቡ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ቡድን 18 ጨዋታ አድርጎ በሚያስመዘግበው ውጤት ነው ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚገባው። ይህ በጣም ትንሽ ነው ፤ በፕሮጀክት ደረጃ እንኳን ከዚህ በላይ እንዲጫወቱ ነው የዕድሜ እርከኑ የሚጋብዘው። ቢያንስ ምድቡ ለሁለት ቢከፈል እና አንድ ቡድን 28 ጨዋታ ቢያደርግ ከዛም አንደኛ እና ሁለተኛ የሆኑትን ቡድኖች እርስ በእርስ እንዲጫወቱ ቢደረግ በ31 ጨዋታዎች የተፈተነ ቡድን ቢያልፍ ጥሩ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።”

አሁን ባለው የውድድር ቅርፅም ቢሆን ግን የንግድ ባንክ እየተሻሻለ መምጣት የረፈደ ነበር ማለት አይቻልም። ምክንያቱም በሁለተኛው ዙር ያሳየው መነቃቃት ዛሬ ላይ ከመሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የአንድ ነጥብ ልዩነት ላይ እንዲገኝ የማስቻል አቅም ነበረው። ሆኖም በዙሩ ባንክ በሀላባ ያስተናገደው ብቸኛ ሽንፈት ከመሪው ጋር ያለውን ርቀት አራት ላይ እንዲቆም ማድረጉ ቁጭት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። አሰልጣኝ ደግአረገም በዚህ ዙርያ የሚሉት አላቸው።

” እግርኳስ ላይ ቁጭት ሁሌም ያለ ነው። እዚህ ባህር ዳር ከመጣን በኋላም ከሀላባ ጋር የጣልነው ነጥብ እጅግ ያስቆጫል። በእግርኳስ ወጥ የሆነ አቋም ይዞ ለመዝለቅ ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው ፤ ሁሌም አይሳካም። አንዳንዴ በዕለታዊ ብቃት እንደቡድን የምትወርድበት አጋጣሚ ይፈጠራል። የውድድር ስፖርት ስለሆነ የምትጥላቸው ነጥቦች በኋላ ላይ ዋጋ ሲያስከፍሉህ ታያለህ። መጀመሪያም ጥሩ ነጥብ ሰብስብህ በኋላ ላይ የምትጥል ከሆነ ጫና ውስጥ መግባትህ አይቀርም። እነዛ ነገሮች ያስቆጫሉ። በአንደኛው ዙር በዘጠኝ ጨዋታ 13 ነጥብ ይዘን ነው የጨረስነው አሁን ግን በስድስት ጨዋታዎች 15 ነጥቦች ሰብስበናል። እንደ ክለብ የቀሩንን ጨዋታዎች አሸንፈን የመጨረሻ ውጤታችን የሚያደርሰን ቦታ ላይ መድረስ ነው የምናስበው። በጥሩ ተነሳሽነት እና መንፈስ ውድድሩን እያካሄድን ነው። የተጫዋቾቻችንን ሥነ ልቦናም በጣም ጥሩ ነው። ”

ሰኞ 4፡00 ንግድ ባንክ ከነጌሌ አርሲ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል። ይህ ጨዋታ የሁለቱንም የውድድር ዘመኑን ጉዞ መዳረሻ የመወሰን አቅም ያለው በመሆኑ ከፍ ባለ ትኩረት ጨዋታውን እንደሚከውኑ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ግን ለሌላው ቡድን ከሚሰጠት ትኩረት የበለጠ እንደማይሰጡት ይናገራሉ። ” ከነጌሌ አርሲም ሆነ ከሌላ ቡድን ጋር የሚገኘው ነጥብ ያው ሦስት ነጥብ ነው። ነገር ግን ዕኩል ነጥብ ላይ መገኘታችን እና ለቻምፒዮንነት ተፎካካሪ እንደመሆናችን መጠን ጨዋታው ላይ የሚመዘገበው ውጤት እጅግ ያስፈልገናል። የሚያሽንፈው ቡድን ወደ ፊት ሲፈነጠር የሚሸነፈው ደግሞ ባለበት ነው የሚቀረው። ስለዚህ ለእያንዳንዱ ጨዋታ በምንሰጠው ትኩረት ልክ ለነገሌም ትኩረት ሰጥተን ነው የምንገባው። ነገሌ ጠንካራ ቡድን ነው። እስካሁን በመጣበት መንገድ ወስጥ ወጥ እንቅስቃሴ ለማሳየት የሚጥር ቡድን ነው። ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን የያዘም ቡድን ነው። ተገቢውን ክብር ለተጋጣሚያችን እንሰጣለን። ነገር ግን በዘጠና ደቂቃ የሚወሰን ውጤት ነው የሚሆነው። እንደቡድን ተገቢውን ዝግጅት እያደረግን ነው እነሱም ጠንካራ የሆነውን ነጌሌን ይዘው እንደሚቀርቡ እናውቃለን። ሁለተኛው ዙር ላይ ከሌሎቹ ቡድኖች የተሻለ ነጥብ ሰብስበናል። ይህ ደግሞ እኛም ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረግን እንደሆነ ያሳያል። ይህንኑ አስጠብቀን ለመጓዝ ጥረት እናደርጋለን።” ብለዋል።

ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ተስፋው የተንጠለጠለው በኤሌክትሪክ ውጤት ላይ ቢሆንም ለመሳካት እየሠሩ እንደሆነ የሚገልፁት አሰልጣኝ ደግአረገ አሁንም ይህንን የማሳካት ዕድሉ እንዳላቸው ያምናሉ። ”ይህ ምድብ ጠንካራ ምድብ ነው። ለምሳሌ አምቦ በነጥብ ታች ያለ ቡድን ነው ነገር ግን መሪው ኤሌክትሪክን ነጥብ አስጥሏል። ሀላባ አጣብቅኝ ውስጥ ሆኖ እየተጫወተ ቢሆንም ከእኛ ሦስት ነጥብ ወስዷል። ዲላ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ነው ያለው ግን ነጌሌ አርሲን ነጥብ አስጥሏል። ስለዚህ እያንዳንዱ ጨዋታ ይሄ ጠንካራ ነው ይሄ ደካማ ነው የሚባል ዓይነት አይደለም። ሁሉም ቡድን ጠንካራ ነው። ከሦስቱ ምድቦች ባለን መረጃ ጠንካራው ይሄ ምድብ ነው። በእያንዳንዱ ጨዋታም ምን እንደሚፈጠር መገመት ከባድ ነው። ስለዚህ እኛ የራሳችንን የቤት ሥራ መወጣት ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው። ፊታችንን ያሉ ጨዋታዎችን ውጤታማ ሆነን ለመውጣት ያለንን ብቃት ጫፍ እንጠቀማለን። በሌላ ጎኑ ደግሞ መሪ ላይ ያለው ቡድን ነጥብ ሊጥል የማይችልበት ምክንያት የለም። ያ ደግሞ የእኛን ወደ ፊት መሄድ ያፋጥነዋል ማለት ነው። ምንም እንኳን በሌሎች እጅም የሚወሰን ቢሆንም የምችለውን እናደርጋለን። ኤሌክትሪክ በአራት ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው። ይሄም ዕድሉን በራሱ የመወሰን ጥቅምን ይሰጠዋል። ከእሱ ታች ያለነው ደግሞ የራሳችንን የቤት ሥራ እየተወጣን የኤሌክትሪክን ነጥብ መጣል መጠበቅ የግድ ይለናል። በስሌት ደረጃ ግን ዕድሉ አሁንም ክፍት ነው።” በማለት በከፍተኛ ሊጉ ተገማች አለመሆን ምክንያት አሁንም ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ዕድሉ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ወደ ወንዶች እግርኳስ ባልተጠነቀ መንገድ የተመለሰው ንግድ ባንክ ዕቅዱ በአጭሩ ሰምሮ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ይቀላቀል ይሆን ?