“በቀጣይ እጅግ ብዙ ሥራ ነው ያለብን” እንዳልካቸው ጫካ

የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

በሕንድ ለሚደረገው የ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ዩጋንዳን በደርሶ መልስ የ3-3 ውጤት ከሜዳው ውጪ በተቆጠረ ጎል ማለፍ የቻለው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ከዛሬው የመልስ ጨዋታ በኋላ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው 

“ጥሩ ነው ፤ ባመጣነው ውጤት ደስ ብሎናል። የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው። ጨዋታው ግን እንደጠበቅነው አልነበረም ፤ እንደዚህ አልነበረም የነገርናቸው። ትንሽ ተጫዋቾቼ ላይ ክፍተት ነበር። በቀጣይ ክፍተቶቻችንን እናስተካክላለን። በመጣው ውጤት ግን በጣም ደስ ብሎኛል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ስለተወሰደባቸው ምክንያት

“ተጫዋቾቼ ወደ ኋላ አፈግፍገው ነው ለመጫወት የፈለጉት። ይህም የሆነው ነጥቡን አስጠብቆ ለመውጣት ነው። ይህ በመፈጠሩ ምክንያት ዩጋንዳዎች ብልጫ ወስደውብናል። ያላቸው አማራጭ ማሸነፍ ነበር። የእኛ ተጫዋቾች ደግሞ እንዳልኩት ወደ ኋላ አፈግፍገው ትንሽ መረጋጋት አልነበረባቸውም። ከዕረፍት በኋላ ከነገርናቸው በኋላ ነው ተረጋግተው ውጤቱን ይዘን ልንወጣ የቻልነው።

ቡድኑ ላይ ስላለው ክፍተት

“ልክ ነው ፤ በቀጣይ እጅግ ብዙ ሥራ ነው ያለብን። ብዙ የምናስተካክላቸው ነገሮች አሉ። የምንገጥማቸውም ቡድኖች በጣም ጠንካሮች ናቸው። ክፍተታችንን በደንብ አይተናል። ስለዚህ በቀጣይ በደንብ እንሰራለን።”